Monday, August 17, 2009

ከከበሮ መቺነት እስከ ሙዚቃ አብዮተኝነት


ካሳሁን ገርማሞ በ1939 ዓ.ም አዲስ አበባ ተወለደ ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ዘነበች አንጩ፣ አባቱ ገርማሞ ወናዬ ይባላሉ፡፡ ካሳሁን አዲስ አበባ ይወለድ እንጂ ያደገው ግን ተፈሪ ኬላ በምትባል አገር ነው፡፡ እድሜው ለትምህርት እንደደረሰም ተፈሪ ኬላ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ትምህርቱን መከታተል ጀመረ እዚያው ትምህርቱን በመከታተል ላይ እንዳለ ቤተሰቦቹ ተመልሰው ወደአ/አ በመምጣታቸው እሱም ወደ ትውልድ አገሩ ተመለሰ፡፡ አ/አ መጥቶ ልዑል መኮንን ት/ቤት ትምህርቱን መከታተል ጀመረ፡፡
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገባ በተማሪዎች መማከርት በነበረው ንቁ ተሳትፎ ‹‹የባለታሪካችንን›› ገፀ ባህሪይ ወክሎ ተማሪዎች ፊት መታየት ጀመረ፡፡ በግጥሞችም የሁለገብ ችሎታውን አሳየ፡፡ ካሳሁንም እንዲህ እያለ ትምህርቱን ጨረሰ፡፡ ትምህርቱን ጨርሶ ግን አልቆመም ቀጥታ ያመራው ወደ ፖሊስ ሙዚቃና የቴአትር ክፍል ነው፡፡ በወቅቱም እንደርሱ ያለ ሰው ያስፈልግ ስለነበር ታህሳስ 1961 ዓ.ም የቅጥር ውል ፈጽሞ በቋሚነት ስራውን ጀመረ፡፡
እዛም በመስራት ላይ እያለ ለታዋቂ ድምጻዊያኖች ግጥምና ዜማ በመስጠት ይታወቃል ግጥምና ዜማ ከሰጣቸው ድምጻዊያኖች መካከል ሒሩት በቀለ፣ ታደለ በቀለ፣ በኃይሉ እሸቴና ተስፋዬ በላይ…በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹ካሳሁን ከመድረክ አስተዋዋቂነት ጎን ለጎን ግጥም ይጽፋል፣ ዜማ ይደርሳል፣ አዳዲስ የውዝዋዜ ስልቶችን ያወጣል፣ ሙዚቃ አሬንጅ ያደርጋል የመድረክ አስተዋዋቂ ነው ቀልድና ቁምነገር በአንድ ላይ ማዋሀድ ይችልበታል፡፡
በ1960ዎቹ ዓ.ም በፖሊስ ሰራዊት ሙዚቃና ቴአትር ክፍል ውስጥ ካሳሁን ገርማሞ መድረኩን ሲመራ ጥላዬ አራጌ ስትወዛወዝ ሁለቱም ወጣቶች ለፍቅር ተጫጩ፤ የመድረክ ተወዛዋዥ ጥላዬ የተመልካችን አይን ብቻ ሳይሆን ካሳሁንንም ቀልብ ገዛች፡፡ እሷም በልዩ የመድረክ አቀራረብ ለዛው ተሳበች ተፈላለጉ ተዋደዱ ጐጆ ለመቀለስ ወሰኑ፡፡
በሐምሌ ወር 1967 ዓ.ም የጋብቻ ስነስርዓታቸውን ፈጸሙ
በሐምሌ ወር 1968 ዓ.ም ቴዎድሮስ ካሳሁን ተወለደ
v ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ስለአባቱ ከተናገረው፡-
አባቴና እናቴ የተገናኙበትን ጊዜ በትክክል ባላውቀውም መስሪያቤታቸው አንድ ላይ መሆኑን አውቅ ነበር እሱ የመድረክ መሪ እሷ ደግሞ የመድረክ ተወዛዋዥ ነበረች፡፡ የተጋቡት በ1967 ዓ.ም ነው እናቴ ጥላዬ አራጌ የ17 ዓመት ወጣት ነበረች፡፡ እርሱ ደግሞ ወደ 20ዎቹ መጨረሻ ነበር ሲሉ አውቃለሁ በተጋቡ በአንድ አመታቸው እኔ ተወለድኩኝ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ብዙ አመት አብረው አልኖሩም የተለያዩበትን ቀን በትክክል ባላውቀውም ለ6ኛ የልደት ቀኔ እለት ግን እናቴ አልነበረችም፡፡ አባቴ ከዚያ በኋላ ለራሱ አልኖረም እናትም አባትም ሆኖ አሳደገኝ የኖረው ለኔ ነበር፡፡ ጥሩ ትምህርት ቤት አስተምሮኛል፡፡ በዘመናዊ አስተዳደግና በጥሩ ስነምግባር አሳድጐኛል።
አባቴ ሙዚቀኛ እንድሆን ፈጽሞ አይፈልግም አስቦትም አያውቅም ምክንያቱም በነሱ ዘመን በኪነጥበቡ አካባቢ የነበሩ ሰዎችን በኑሮ ውጤታማ አለመሆንን በማየት ይመስለኛል በተጨማሪም ልክ የምስራ ሳይሆን የማጠፋ ስለሚመስለው የኔን ሙዚቀኝነት አልወደደውም ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን የስራ ውጤቴን የኔንም ስነስርዓት ሲያየው ሞያዬን እየተቀበለው መጥቶ ነበር፡፡ ግን መጨረሻውን ሳያየው ቀረ የምወደው አባቴ በ1993 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡
‹‹ከአርቲስት ቤተሰብ መፈጠሩ ደስ ይለኛል››
ክቡር ዶ/ር ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ
አባቱ ካሳሁን ገርማሞ የፖሊስ ኦርኬስትራ አስተዋዋቂና የፖሊስ ፕሮግራም ጋዜጠኛ ነበር፡፡ እናቱ ወይዘሮ ጥላዬ እዚያው ክፍል ውስጥ በተወዛዋዥነት ሰርታለች፡፡ ቴዎድሮስ ከአርቲስት ቤተሰብ በመፈጠሩ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ከዚያ ቤተሰብ ወጥቶ ለዚህ መብቃቱ እጅግ ያኮራል፡፡ ልጁን እንደተመለከትኩት የእድሜ ማነስ ሳይሆን ቁም ነገር ያለው ተግባር ለመፈጸም እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ በድምጹም ሆነ በስራው አደንቀዋለሁ፡፡ ሊሰራ የፈለጋቸውን ነገሮች ሁሉ አስቦ በራሱ ዜማ፣ በራሱ ግጥም፣ በራሱ ድምጽ አገናኝቶ መሰራት የሚችል ብቁ አርቲስት ነው ማለት እችላለሁ፡፡
‹‹ዘውድ ብጭንና ቢዘፍንልኝ አልጠላም››
አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁ የማስታወቂያ ስራ ባለሙያ
ስለሱ ለመግለጽ በቂ ሀይል ያለው ቃል የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ልጁ’ኮ ከስንት አንዴ ብቅ የሚል ውብ ጀምበር ነው፡፡ ባቀረባቸው አራቱ ምርጥ የመታሰቢያ ስራዎች፣ ለኃይሌ፣ ለግርማዊነታቸው፣ ለቀነኒሳና ለቦብማርሌ በዘፈናቸው ስራዎች እንዳከብረው አድርጐኛል፡፡ አጥንት ሰብረው ይገባሉ አእምሮው ከዘፈነላቸው ሯጮች በላይ እንደሚፈጥን ይሰማኛል፡፡
አእምሮህን እወደዋለሁ፡፡ ሸራተን ሆቴል መድረክ ላይ ሲጠየቅ በቅርብ አይቼዋለሁ፡፡ የመልሱ ፍጥነት ችሎታውን ገላጭ ነው፡፡ ምኞቴ፤ በዓለም ላይ የማይጠገቡ አራት ነገሮች አሉ፡፡ ሀብት፣ እድሜ፣ ስልጣንና ፍቅር እንዲያገኝ ነው፡፡ ልጁ ደግሞ ገንዘብ፣ ውበት፣ ዝና ወጣትነትና ብስለት አለው፡፡ ፍጹም ለትዳር የተመቸ ነው፡፡ ግብዝ አይደለም፡፡ ቢሆንማ ኖሮ እስካሁን ይበላሽ ነበር፡፡ በመጨረሻም ዘር ቆጥሬ ‹‹ዘውድ›› ብጭንና ቢዘፍንልኝ አልጠላም።
‘በከበሮ ጀመረ ዛሬ ለዚህ በቃ’
- አጐቱ አቶ ሃይሉ ገርማሞ
የልጅነት ምኞቱ ምን ነበር?፦ የማትለየው ትንሽ ከበሮ ነበረች፡፡ እሷን ሁሌ ይደልቃል፡፡ ዘፍነህ የት ልትደርስ ነው; እለው ነበር፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ያውቃል፤ አንድ ቀን ታየኛለህ›› ይለኛል፡፡ያሳደገችው እህቴ ለፀጉር መቀጠያ ያመጣችውን አርቴፊሻል ፀጉር አፄ ቴዎድሮስን ሆኖ ለመስራት ከቤት ይዞ ጠፋባትና ስለምትወደው ተወችለት፡፡ በከበሮ ጀመረ ዛሬ ለዚህ በቃ፡፡
‹‹የሳይንስ ትምህርት ፍላጎት ነበረው››
መምህሩ ሐጎስ አርአያ
ቤቴልሔም ትምህርት ቤት ውስጥ 6ኛ ክፍል ሳይንስ አስተምሬዋለሁ የሳይንስ ትምህርት ፍላጐት ነበረው፡፡ በክፈለ ጊዜው ለእረፍት ያህል መሐል ላይ መዝናኛዎች አይጠፉም የልብና የአንጀት ስዕሎች ሳቀርብ ቴዲ በግጥም ይገልጻቸዋል፡፡ ንቁ ተማሪ ነው፡፡ እያዝናና ጭንቅላታቸው ውስጥ እንዲቀረጽ ያደርጋል፡፡
ወደሌላ ክፍል እወስደውና ያነብላቸዋል በዚህ ምክንያት ሁሌም ተሰጥኦ እንዳለውና እንዲገፋበት እነግረው ነበር፡፡በትምህርት ቤት ክበባት ውስጥ በስነጽሁፍ ጥያቄና መልስ ውድድር ላይ ይወዳደራል ግጥሞቹንም በዘፈን መልክ ያቀርባቸዋል፡፡ አድጐ ‹‹ባይገርምሽ ገና እወድሻለሁ›› እያለ በቴሌቪዥን ሲጫወት ማየቴ ትንግርት ሆነብኝ ‹‹ይህ ልጅ ትልቅ ሰው ሆነ›› አልኩኝ፡፡ ከዘፈኖቹ ‹‹ታሪክ ተሰራ›› እና ‹‹ባይገርምሸን›› እወዳቸዋለሁ ‹‹አቡጊዳንም›› የራሱን ስልት ካሳየባቸው ስራዎች አንዱ ነው፡፡ ወደፊት የሱዳንና የጃፓን ስልቶችን በሙዚቃው ውስጥ ቢያካትት እመርጣለሁ፡፡
‹‹ቴዲ ችሎታ ያለው ድምጻዊ ነው››
አቶ አዲሱ ገሠሠ (የቴዎድሮስ ካሳሁን ማኔጀር)
ከጂጂ ጋር ብቻ ነበር የሰራነው፡፡ ተሰጥኦ ስላላት በዓለም ላይ ላስተዋውቃት ሞክሬያለሁ፡፡ ቴዲን በመጀመሪያ ወደ አሜሪካን ወሰድኩት፡፡ ዋሽንግተን ባቀረበው ስራ ተስፋ እንዳለው አወቅሁ፡፡ ከብዙ ሰዎች ጋርም አስተዋወቅሁት ተሰጥኦውን እንዲያውቁለት፣ ችሎታውን እንዲያደንቁለት አደረኩ፡፡ ከዚያም ወደአረብ ሀገራት በመሔድ የተለያዩ ዝግጅቶችን አቅርቧል፡፡
በዘፈኑ በኩል አንዳንዴ ትንሽ ልጁን ያለመረዳት ችግር እንዳለ አይቻለሁ፡፡ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰርቷል፡፡ ያው እንደተለመደው ብዙዎቹ የኪነጥበብ ሰዎች የሚያቀርቧቸው የፈጠራ ስራዎች በተሳሳተ መንገድ እንደሚተረጎምባቸው አውቃለሁ፡፡ ቦብ ማርሌም ይህ ደርሶበታል፡፡ ቴዲ ችሎታ ያለው ድምጻዊ ነው፡፡ በቀረበበት መድረክ ሁሉ ተቀባይነቱ እጅግ የደመቀ ነበር፡፡
እሱን ይዤ በመስራቴ እደሰታለሁ፡፡ በተለይ ስራዎቹን ከቤተሰቦቼ ጋር ሆነን ስናየው የተለየ ስሜት አሳድሮብናል፡፡ እንደእኔ አስተያየት አልበም ማውጣት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የሰዎችን ፍላጐት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከተለያዩ አርቲስቶች ጋር እንደመኖሬ ቴዲ ለየት ይላል፡፡
ሙዚቃ ህይወቴ ወ ካሣ መንፈስ በቱባው ቋንቋ
ተው ልጄ ኪነት- ከሀሁ ታረቅ
በአንቺ ሆዬ ቃና- ዮራይስመሌ (በጉራጊኛ)
በትዝታ ቃና- ፈርዲዳ ማሣርቦ
በአንቺ ሆዬ ቃና- ደርፊ ምስ ጓላይ (በትግሪኛ)
ቶሌ ቶሌ ያሚ ጋሪ ናቃሪ ፈያ (በኦሮምኛ)
ወላይታ ካአ (በወላይትኛ)
ሙዚቃ ህይወቴ ግዕዝና ዕዝል አራራይ
የተሰጠች ከላይ
ያሬዳዊ ስልቱ የሰማይ ፀጋ
አቆራኘኋት ነፍሴን ከአንቺ ጋ፡፡
በአገሬ ቅኝት የብሔር ቋንቋ
እደሰታለሁ እኔ አላዝነም በቃ፡፡
በአፋር ሲዳማ በጋምቤላ ቶም
ልርገጥ ዳንኪራ እኔ አላዝንም ከቶም፡፡
መሀያበያባ መሃያበያባ (በአፋርኛ)
ሃያባያ መሃያበያባ
ሀያብዬ እኔስ ለአብዬ፡፡
ሙዚቃ ህይወቴ ግዕዝና ዕዝል አራራይ
የተሰጠች ከላይ
ተው ቢል አልሰማ በልጅነቴ
ገርፎ ሲቀጣኝ ሲመክረኝ አባቴ
ስንት ያየሁብሽ ሙዚቃ ህይወቴ
ቆመህ ካላየህ አታምንምና
ላባብልህ ዛሬ በክራሬ ቃና
ለሟች ማዘን የለም
ባለው መጽናናት ነው ብለህ እንዳስተማርከኝ
ባንተው ምክር ሄጄ በአንተው አስጨከንከኝ
እሱ እንዳለው ያ ሎሬቱ
ሞትም ይሙት የታባቱ
በሞትህ ላይ ፎክሬበት በዳንኪራ
ትነሳለህ ከእኔ ጋራ
መሀያበያባ መሃያበያባ ሀያብዬ
አልሞትክም አብዬ
መሃያበያባ መሃያበያባ ሃያብዬ
እኔ አለሁ አብዬ፡፡
ሙዚቃ ህይወቴ ግዕዝና ዕዝል አራራይ
የተሰጠች ከላይ
በዚህ ኑሮ ብሎ ከላይ ካዘዘ
ልጁ ምን ያድርግ ክራሩን ያዘ፡፡
አትዘንበት አደራ አብዲ (አባቴ)
ማርኮት ቅኝቱ ምን ያድርግ ኧዲ፡፡ (እኔ)
መሃያበያባ መሃያበያባ
ሃያባያ መሃያበያባ
መሃያበያባ መሃያበያባ ሃያብዬ
ጀነቱን ለአብዬ፡፡
በቴዎድሮስ ካሳሁን (በቴዲ አፍሮ)
‹‹ስራዎቹ የላቀ ኢትዮጵያዊ ስሜት አላቸው››
ተዋናይ፣ ፀሐፌተውኔት፣ አዘጋጅና ገጣሚ ጌትነት እንየው
የግጥሞቹ ይዘት፦ የቴዲ የዘፈን ግጥሞች፣ ይዘታቸው፣ ስፋት አላቸው፡፡ ከሌሎች ከምንሰማቸው በጾታ ፍቅር ርዕስ ላይ ከሚያጠነጥኑት የላቀ ነው፡፡ ወደኋላ ታሪካዊ የሆኑ ድርጊቶችን ያነሳሉ፡፡ ጀግኖች ያወድሳሉ፡፡ ስለ አፄ ኃይለስላሴ፣ ስለኃይሌ ገብረስላሴ፣ ‹‹እንደየሩሳሌም›› የሚለውና ስለሩጫው የሰማነው ሁሉ ብሔራዊ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ናቸው፡፡


ጭብጦች፦ የሚያነሳቸው ጭብጦች በፍቅር ብቻ የተወሰኑ አይደሉም፡፡ ብሔራዊ ማንነትን ይገልጻሉ፡፡ ይሔ A,B,C,D የሚለው የእኛ አቡጊዳ ነው ከልጅነት የህይወት ያህል ይሰፋል፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ስሰማው ያኔ ቁምጣ ለብሼ ቄስ ትምህርት ቤት ውስጥ በጅራፍ ተገርፌ አንገቴ ያበጠውን አስታውሳለሁ፡፡ ስራዎቹ የላቀ ኢትዮጵያዊ ስሜት አላቸው፡፡ በአንድ ምሽት እንደዚያ በጣም ስሜት የሚቀሰቅስ ጽሁፍ ድንገት የሚመጣ አይደለም፡፡
አቀራረብ፦ ከህጻናት እስከ ሀገር መሪዎች ድረስ ያደነቁት ሰፊና ታሪካዊ የሆኑ ጭብጦችን በቀላል ቋንቋ የመግለጽ ብቃት ስላለው ነው፡፡ ምናባዊ፣ ውስጣዊ የሚል ትርጓሜ ኖሮት ቃላቱ ሲፈቱ አይከረሙም፡፡ ይሰማል ይገባል፡፡ በቀላል ቋንቋ ለመግጠም የራስ የሆነ ብቃት ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ መንግስቱ ለማቀላል በሆኑ ቃላት፣ ቀለል ባሉ አገላለጽ የሚያፈላስፉ ጉዳዮችን ያነሳሉ፡፡ ቀላልና ተራ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ቀለል ያለው ቋንቋ አጠቃቀም ሙዚቃ ወዲያው እንዲገባ ይረዳል፡፡ እንደ መንግስቱ ለማ ጥልቅ ሀሳብን በቀላል ቋንቋ የሚያቀርቡ ጥቂት ናቸው፡፡ በዘፈኑ በኩል ቴዲን አግኝተናል፡፡
‹‹እስካሁን እንድሮጥ አድርጐኛል አርጅቼም በከዘራ ሳልሮጥ አልቀርም!››
አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ (ክቡር ዶ/ር)
• ዘፈንና ስሜት፦ - ‹‹አልሆንልህ አለኝ›› የሚለው ዘፈኑ ከምስል ጋር ተቀናብሮ መታየቱን ነገሩኝ፡፡ ያኔ አቴንስ ነበርኩ፡፡ ዜማውን በመጠኑ በስልክ አሰሙኝ፡፡ ብዙም ጥራት አልነበረውም፡፡ ስመጣ ከቤተሰቦቼ ጋር ተመለከትኩት ያስለቅሳል፡፡ ውስጤ የሆነ ነገር ተላወሰ፡፡ ያንን መግለጽ ይከብደኛል፡፡ ስሜትን ይረብሻል እውነተኛ ህይወት ውስጥ ይከታል፡፡ የሚደነቅ አይነት ነበር፡፡ ያንን እያየሁ መተኛትም ሆነ መቀመጥ አልነበረብኝም ኦፕራሲዮን ሆኜ ሮጫለሁ፡፡
• የዜማ ኃይል፦ - ‹‹መርቆ ሸኝቶ ሀገር›› የሚለው ይስበኛል፡፡ ሽማግሌው ሲመጡ ሳይ፣ ቀነኒሳ ወደኋላ እየዞረ ሲመለከት ‹‹አንተን ጥሎ መሔድ…›› ሲል እነሱ ቦታዎች በጣም ይረብሹኛል፡፡ በመጀመሪያ ስለ እኔ በዘፈነው እስካሁን እንድሮጥ አድርጐኛል ለዚህ ደግሞ እኔ እንጃ አርጅቼም በከዘራ ሳልሮጥ አልቀርም፡፡
‹‹እውነትን በዜማ ይነግረናል›› ደራሲና የፊልም ዳይሬክተር ተስፋዬ ማሞ
ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ምን ያህል ተዋህደው እንደሚኖሩ አንድ ምሳሌ ላንሳ፣ ወሎ ውስጥ አንድ ቤተክርስቲያን አለ፡፡ ስሙን ካልተሳሳትኩ ሩጋ ሚካኤል ይባላል፡፡ እዚያ የሚኖሩት አብዛኞቹ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ቀሳውስቱ በቁጥር ያንሳሉ፡፡ ካህናቱ ቤተክርስቲያኑን ለማስተዳደር አንስተው ደሴ ለማድረግ ያስባሉ:: ይሔኔ የአካባቢው ሙስሊሞች ይቃወማሉ፡፡ ተባብርን የጐለደውን አሟልተን ትኖራላችሁ እንጂ አትሔዱም ብለው ይከለክሏቸዋል፡፡ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ገንዘብ ተዋጥቶ ቤተክርስቲያኑ እስካሁን እዚያው ይኖራል፡፡ ቴዲ ይህንን ነው በጥሩ ቋንቋ የገለጸው፡፡ ይህ ለኛ ብቻ አይደለም ለዓለም ሊሸጥ ይችላል፡፡ ዛሬ በአክሪራነት በግራና ቀኝ አለም በምትተራመስበት ሰዓት ኢትዮጵያ እንደትልቅ ተምሳሌት እንድትቆጠር ያደርጋታል፡፡ በመሆኑም በቴዲ እንኮራበታለን:: በልጅነቱ ያገር ሽማግሌ ስራ እንደመስራቱ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡
‹‹ልቤ መጮህ ይፈልጋል›› ትርፌ ማንያህልሃል /ዲጄ ኪን/
ቴዲ በግጥሞቹ፣ በዜማዎቹ እና በቅላጼው ትልቅ ስራ አበርክቷል፡፡ በዘፈኑ ብዙ ነገሮች ማካተትን ችሏል፡፡ ቴዲን እንደጥላሁን ገሠሠ ነው የማየው በስሜት ነው የሚዘፍነው፡፡ የሰውን የልብ ትርታ የሚያውቅ ይመስለኛል:: ለዚህም ሳይሆን አይቀርም አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ዘፈኖቹን ያዳምጣቸዋል፡፡
እኔ አስከማውቀው ድረስ ለቦብ ማርሌ አድናቆት አለው፡፡ ከልቡ ይወደዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የሬጌን የሙዚቃ ስልት ሲሞከር አይቸዋለሁ፡፡ በእርግጥ የጀማይካ ሳይሆን የኢትዮጵያ ስልት ይጐላበታል፡፡ እናም የኛን ፈጥሯል ማለት እችላላሁ፡፡ ቴዲ ስለዘፈኑ ሲነግረኝ ልቤ መጮህ ይፈልጋል ይለኛል፡፡ እግዚአብሔር በሰጠኝ ተሰጥኦ ለህዝቡ ማገልገል አለብኝ ይላል፡፡

No comments: