Thursday, December 4, 2008

ቴዲን የፖለቲካ እስረኛ የሚያስመስሉት 8 ነጥቦች



1 የቴዲ አፍሮ ጉዳይ ፖለቲካዊ መምሰሉና ጠበቃው አቶ ሚሊዮን አሰፋ የኢህአዴግ ደጋፊና የምርጫ ቦርድ ጠበቃ ሆኖ፣ የቅንጅት አመራሮች እስር ቤት በነበሩበት ወቅት እስሩን ደግፎ ሞት ሊፈረድባቸው ይገባል እያለ በመንግሥት ራዲዮና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በየቀኑ መግለጫ ሲሰጥ የነበረ ጠበቃ መሆኑ፤
2 ሁለተኛ ወንጀል ችሎት የነበሩትና ለሁለት ዓመታት የዘለቀውንና የቅንጅት አመራሮች ... የተከሰሱበትን ችሎት በቀኝ ዳኝነት ሲያስችሉ የነበሩት አቶ ልዑል ወ/ማርያም በድንገት 8ኛ ወንጀል ችሎት መገኘት፤ (አቶ ልኡል ለበርካታ ጋዜጠኞች መሰደድ: መታሰር እና መታረዝ ዋና ምክንያት ነው::) ሰሞኑን አዲስ አበባ ከተማ በተደረገው የታላቁ ሩጫ ውድድር ላይ የቴዲን ስም የጠሩና ፎቶ ግራፉ ያለበትን ቲሸርቱን የለበሱ መታሰራቸው፤ በኢንጂነር ሃይሉ ሻውል የሚመራው መኢአድ በአዲስ አበባ አደባባዮች የመኪና ላይ ቅስቀሳ ሲያደርግ በቴዲ አፍሮ ሙዚቃዎች እንዳይቀሰቅሱ መከልከላቸው፤
3 ምኒልክ ሆስፒታል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኦርጅናል የአስከሬን የምርመራ ውጤትን 'ተሳስቷል' በሚል መቀየሩ፤
4 ችሎት በሚኖርበት ጊዜ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደህንነቶች ችሎቱን ማጨናነቃቸውና ችሎት ተከታታዩን ሰው ማስጨነቃቸው፤
5 በቴዲ የፍርድ ቤት ንግግር ያለቀሱ አድናቂዎቹ መታሰርና መንገላታት:
6 የቅንጅት አመራሮችን ሲጠብቁ የነበሩ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊሶች ሳይታክቱ በችሎት በመገኘት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረጋቸው፤
7 ቃሊቲ ከገባ በኋላ ለብቻው መታሰሩ፤
8 ከተወሰኑ ሰዎች በስተቀር ማንም እንዳይጠይቀው መከልከሉ፤ በመኪና ሰው ገጭተሃል በሚል ተጠርጥሮ ለታሰረ ሰው ያልተለመዱ ድርጊቶች ናቸው።

የጋዜጣችን ፊት ገጽ


'ሴት ያሳደገው ልጅ ከመባል ዘወትር ለማኝ ሆኖ አባቴ ባይጠቅመኝም ይቅር'



''ይህው ደረትሽ ነው ያጣላኝ ሁሉን !' እስኪ ሽፈን አርጊው ያ ጡት እንደሆን !!'
ይህን ስንኝ የሚረሳ ማነው ? በኢትዮጵያ ራዲዮ ከምሽቱ አራት ሰአት በኍላ የሚተላለፉ የታምራት የሙዚቃ ክፍለጊዜዎች ላይ ሳንሰማቸው የቀረንባቸው ጊዜያት አሉ ? ''ተማር ልጄ '' የምትለውን ሙዚቃም አንረሳም :: እናትና አባቶቻችን በትምህርታችን እንድንበረታ ይህችን ዘፈን እያቀነቀኑ አልመከሩንም ?... የዛሬው የመጀመሪያው ዝግጅቴ ተወዳጁና ተናፋቂውን አርስቲስት አለማየሁ እሸቴን ያስቃኛል :: መልካም ቆይታ :-

ከሊሊ ሞገስ
(የሐበሻ ጋዜጣ ልዩ ጸሐፊ)

''ኢትዮጵያዊ ኤልቪስ ፕሪስሊ '' ይሉታል የዛ ዘመን ሰዎች :: በሙዚቃ ሥራው በዛም ዘመን በእኛም ዘመን አዲስ ና ልዩ እንዲሁም የራሱ ፈጠራ ያለው ሰው ሆኖ እዚህ ደርሷል :: ''አዲስ አበባ ቤቴ ... አዲስ አበባ ቤቴ ሸጋ ልጅ ቆንጆ ልጅ አለች ጎረቤቴ ''
ታዋቂው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ''አለማየሁ እሽቴን እንዴት አድርገህ ትገልጸዋለህ ?'' በሚል መነን በሚባል መጽሄት ለቀረበለት ጥያቄ ትንሽ ቆም ብሎ በማሰብ ''ሦስት ነግሮች አሉት '' ሲል ይጀምራል :: ''አለማየሁ የራሱ የሆነ ፈጠራ አለው :: ከሁሉም ዘፈኞች ወጣ ያለ ባህሪ እንዲኖረው ይፈልጋል :: ከዚህም በላይ ለአዲስ ነገር ቅርብ ነው '' ሲል ይገልጸዋል :: ይህ የጥላሁን ገለጻ በእርግጥም ትክክል ነው :: በሾላ አካባቢ በገዛው መሬት የሚኖረው አለማየሁ እሸቴ አብዛኞቹ የሙያ አጋሮቹ ትዳር እና ሴት ሲቀያይሩ እስኩ ግን እሳካሁን በአንድ ሴት እንደጸና አለ :: በሁለተኛ ደረጃ ለአዲስ ነገር ቅርብ ነው ለሚለው የመጨረሻ ካሴቱን መመልከት ይቻላል :: ከ 2 አመት በፊት በአምባሰል ሙዚቃ ቤት አማካኝነት ያወጣው ካሴቶ እጅግ ተወዳጅ የነበረ ሲሆን በክሊፑም ዘንድ የተዋጣለት መሆኑን አሳይቷል :: በ 3ኛ ደረጃ አሌክስን ልዩ የሚያደርገው ራሱን ከዘመኑ ጋር መለወጡ እና በቆመበት አለመቅረቱ ሲሆን ዘፈኖቹ ከምንም በላይ በምክር እና በትምህርት ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉ ላይ ነው::
''ወደ ሙዚቃው ሙያ ለመግባት መሰት የሆነኝ ለኤልቪስ ያለኝ ፍቅር እና ክብር ነው '' የሚለው አለማየሁ ወደ ሙዚቃው ሕይወቱ ሲገባ በቤተሰቦቹ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ጫና ነበረበት :: በተለይ አባቱ ከሽመል በበለጠ እስከ ጠምንጃ መምዘዝ የደረሱበት ጊዜ ነበር ያኔ :: የዛ ዘመን ሰው ሙዚቀኛን እና ወርቅ አንጣሪን እንዴት ይመለከት እንደነበር ማስታወሱ በቂ ነው:: አለማየሁ ይቀጥላል::
''... በተለይ አባቴ በሙዚቃ ሕይወት ውስጥ ጠልቄ መግባቴን አልወደደልኝም :: ስዘፍን ውዬ ስመጣ ማምሻውን እቤቴ ዱላ ይጠብቀኛል :: የዛን ጊዜ የምንሰራው ለገንዘብ ሳይሆን ለሙያ ፍቅር ነበር :: እናም አንድ ዘፈን አወጣሁ :: ያ ዘፈን :- የሴት ልጅ ከመባል ዘወትር የሚል ነበር :: ይህ ዘፈን መልእክቱ አባት መሞት እንደሌለበት : አባት ከሞተ ልጅ የሴት ልጅ ... ቀማኛ ... ዱርዬ ተብሎ እንደሚሰደብ መልእክት ያለውና የአባትን ጥቅም አጉልቶ የሚያሳይ ነበር :: እናም አባቴ ይህን ዘፈን በራዲዮና በሽክላ ሲሰማ ለሙያዬ ልዩ ፍቅር አደረበት :: መኪና ገዝቶ ሰጠኝ :: ከዛም ያበረታታኝ ጀመር ''
የአለማየሁ የሙዚቃ ሕይወት ጅማሮ ይህን ሲመስል በሙዚቃው ሕይወቱ እውቅናው በመላው ኢትዮጵያ እየተሰራጨ በመጣበት ወቅት በምጽዋ በኩል ጠፍቶ ወደ ሆሊውድ በባህር ጠፍቶ ሊሄድ ሲል ተይዞ መመለሱን ያስታውሳል :: ''ያኔ ወጣት እያለሁ ወደ ሆሊውድ መሄድ ፈልጌ ነበር :: ይህ ህልሜ ቢያሳካ ኖሮ በአለም ላይ ታዋቂ ሰው እሆን ነበር '' ይላል - አሌክስ ::
ከአለማየሁ እሽቴ ጋር በጋራ ለመዝፈን እድሉ ካጋጠማቸው አርቲስቶች መካከል አንዷ ድምጻዊት ኩኩ ሰብስቤ ነበረች :: አርቲስቷ ለአለማየሁ ያላትን ክብር የምትገልጸው በቃል ብቻ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም :: ''አለማየሁ '' ትላለች ''ዳንሱና የዘፈን ግጥሞቹና መልእክቶቹ ደስ ይሉኛል '' ትላለች :: አድናቂው እንደሆነች የምትናገረው ኩኩ አብራው በመዝፈኗ እድለኛ እንደሆነች ጭምር ታብራራለች::
በአራዳ ፒያሳ አካባቢ የቆርቆሮ የሙዚቃ ባንድ ሰርተው የሙዚቃ ጥማቸውን እጃቸው ላይ ልክ ማይክ እንዲመስል እንጨት ወይንም ማንኪያ ይዘው እየዘፈኑ ሙዚቃን የጀመሩት አሌክስና ጓደኞቹ እሱ በሙዚቃው ሥራውን አንቱታን ሲያተርፍ ሌሎቹ ግን በሌላ ሥራ ላይ እንደተሰማሩ ይናገራል :: በግልጽነቱና በትዳሩ ታማኝነቱ በምሳሌነት ከአርቲስቶቻችን የሚጠቀሰው አሌክስ :- በ 1955 ፖሊስ ኦኬስትራ ውዝዋዜ ለመቀጠር /ለመሰልጠን / ሄዳ ፍቅር የሸመተችው እጅጋየሁ እስከዛሬ የአለማየሁ እሸቴ ሚስት ነች ::አለማየሁ እንደ አርቲስት ቀበጥ አይደለም ማለቴ ሲያገባ ሲፈታ የኖረ አይደለም:: ትዳሩን አክባሪ ነው ::በአንድ ወቅት ለትዳሩ እና ለልጆቹ ያለውን አመለካከት ሲነግረኝ ''ለሚስቴም ሆነ ለልጆቼ ያለኝን ፍቅር የሚተካውም ሆነ የሚለውጠው ምንም የለም ::ያለኝን ትርፍ ሰአት ከእነሱ ጋር ባሳልፍ ደስተኛነኝ ""ነው ያለኝ::
''አሁንም ቅድምም ታሽካካለች ዶሮ እኔ አንቺን ማግኘቴ ሕልም ነው ዘንድሮ አዲስ አበባ ቤቴ አዲስ አበባ ቤቴ ሸጋ ልጅ ቆንጆ ልጅ አለች ጎረቤቴ አረ እንዳው ይመኙሻል አረ እንዳው ይመኙሻል በምኞት ቢጓዙ ወዴት ያገኙሻል ''
እኚህ በፎቶ ግራፍ ላይ የምትመለከ ቷቸው ግለሰብ አምሀ እሸቴ ይሰኛሉ :: አምሀ እሸቴ የአባታቸው ስም ከአሌክስ አባት ጋር ሲመሳሰልባችሁ ወንድሙ እንዳይመስሏቸው :: ይልቅዬ በዛ ዘመን ታዋቂ የሙዚቃ አሳታሚ ነበሩ :: በ 1944 የመጀመሪያ የሸክላ ካሴቱን ለሕዝብ ሲያደርስ ሸክላውን ያሳተሙለት እኚሁ ግለሰብ ነበሩ :: አምሀ እሸቴ የሙዚቃ አሳታሚ የሚል ድርጅት የነበራቸው እኚሁ አባት ዛሬ በህይወት አይኑሩ እንጂ ከጥላሁን ገሰሰ ጀምሮ በዛ ዘመን የነበሩ ዘፈኞችን ዘፈኖቻቸውን በሽክላ አሳትመውላቸዋል:: በሙዚቃ ሕይወቱ ከአንድ መቶ በላይ ዘፈኖችን ለሕዝብ ያደረሰው አለማየሁ እሸቴ እስካሁን በካሴትና በሲዲ የሰራቸው ዘፈኖቹ 8 ብቻ ናቸው::
''ኢትዮጵያዊ ኤልቪስ ፕሪስሊ '' አለማየሁ እሸቴ ከአማርኛ ሙዚቃዎች ሌላ የእንግሊዘኛ ሙዚቃዎች የሚዘፍን ሲሆን በተለይም አረብኛ ሙዚቃዎችን በሱዳንኛ ዜማ ይዘፍናል:: ከዚህም በተጨማሪ ሱማሊኛ ይዘፍናል:: አሁን ባለው ሥርአት በእጅጉ የማይወደደው አለማየሁ ለዚህ ምክንያቱ እንደ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች በተለያዩ የተቃዋ ሚ ፓርቲዎች መድረክ በተለይም በአብዮት አደባባይ ከሕዝብ ጋር ለተቃውሞ መውጣቱ በገዢው መደብ ሰዎች ጥርስ እንዲነክስበትና አንዳንድ ጫናዎችም እንዲደረጉበት ሆኗል ::

''ማን ይሁን ትልቅ ሰው ማን ይሁን ትልቅ ሰው ማን ይሁን ትልቅ ሰው ማ .................ን ይሁን ትልቅ ሰው ያንዱን ቁጅ አንደኛው ሲያኮስሰው ማን ይሁን ትልቅሰው .... ያንዱ ቤት ሲጎድል አንዱ እየተረፈው ክፉና ደጉን ዘመን ካሳለፈው እኔ ግን መራመድ ከቶ አልቻልኩም ገና ትኋን !... ትኋን ደሜን መጦ ደሜን መጦታልና ጊዜው ጎዳኝ እንጂ እኔ ሰው አላማም ዋ ... ያህያ ልጅ በቅሎ ወርቅ ተሽልማ ብናገር ወረኛ ባለጌ ይሉኛል ብቻ ግን በሆዴ ቢቀር ይሻለኛል !!
የአሌክስን ይህን ተወዳጅ ሙዚቃ በድምጹ ሲያንቆረቁረው ለመስማት http://www.ethiopianow.com/music/alemayehu/ ላይ 13ኛውን ሙዚቃ ያዳምጡ:: አለማየሁ እሸቴ ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል:: በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላውን ጥበብ አብረን እንቆነጥራለን::ð

ለስለስ ያለች መሳሳም ቁጣን አብርዳ ሰላምን ታሰፍናለች

ከሔኖክ ዓለማየሁ
በሥራ ላይ እድገት አግኝተሽ ወደ ቤት ለመሄድ ቸኩለሻል:: ከመኪናሽ እንዴት እንደወረድሽ ራሱ ትዝ አይልሽም:: ለባለቤትሽ ይህን ታላቅ የምስራች ለመናገርና ደስታሽን አብራችሁ በመፈንደቅ ለማሳለፍ አቅደሻል:: "ፐ አሁን ባለቤቴ ሲሰማ እንዴት ይደሰት ይሆን? መቼም እቅፍ አድርጎ አንገቱ ስር ጠምጥሞ አስገብቶኝ ይስመኛል:: የእኔ ባለቤት እኮ አንበሳ ነሽ ይለኛል" እያልሽ በአይነ ሕሊናሽ እያሰብሽ ነበር መኪናሽን በፍጥነት እየነዳሽ ቤት የገባሽው:: የባለቤትሽን ስም እየተጣራሽ በየክፍሉ ስትፈልጊው ባለቤትሽ የለም:: "ውዴ.. የእኔ ፍቅር... የት ነህ?" እየደጋገምሽ እየተጣራሽ ነው:: ግን ባለቤትሽ በቤት ውስጥ የለም:: በሁኔታው በጣም ተደናግጠሽ ወደ ቤትሽ ጀርባ ስትሄጂ ባለቤትሽ ብቻውን ባልተመለደ መልኩ ተቀምጧል::
እሱን ከቁብ ሳትቆጥሪ ደስታሽን መናገር ቀጠልሽ: ""የሥራ እድገት አገኘሁ እኮ"" ብለሽ ስትነግሪው ባለቤትሽ እንዳሰብሽው ከእቅፍሽ አስገብቶ ሳይስምሽ: ወይም ደስታሽ ደስታዬ ነው ሳይልሽ ጥሎሽ ቢሄድ ምን ትያለሽ?... በትዳርሽ ውስጥ አንድ ትልቅ ችግር አለ ማለት ነው:: ይህን እንዳወቅሽ ከባለቤትሽ ጋር ንትርክ ትጀምሪያለሽ ወይስ ምን ታደርጊያለሽ? የዛሬው የመጀመሪያው የ"ዘ-ሀበሻ" ጋዜጣ የመጀመሪያው እትም የሳይኮሎጂ አምድ ጽፉፌ በስኬታማ ትዳር ላይ ያተኩራል:: አብረን እንቆይ::


በሺዎች የሚቆጠሩ ትዳሮች ውስጥ ባልና ሚስት በቤት ውስጥ የጎሪጥ የመተያየታቸው ነገር ይታያል:: የአብዛኞቹ ትዳር ውስጥ ፍቅር በፍቅረኛነት ዘመን ያለቀ ይመስል አንድ ቤት ውስጥ አንድ ሶፋ ላይ ተቀምጠው ጀርባና ፊት መሰጣጠት የተለመደ ሆኗል:: ሁለታችሁም ከሥራ ገብታችሁ አንቺ ወደ ጓደኞችሽ ደውለሽ ስልክ የምታወሪ ከሆነ እሱም ጋዜጣ ይዞ ተቀምጦ የሚያነብ ከሆነ ፍቅራችሁ ውስጥ መሰለቻቸት የገባ አይመስላችሁም?
አብሮ ተቻችሎ መኖር እጅግ ከባድ ነገር ቢሆንም ይህንን የሚወጡ ባለትዳሮች ከጀግናም በላይ ጀግና አድርገው ሳይኮሎጂስቶች የሚጠሯቸው ለምን ይመስላችኍል?? የሀገሬ ሰው ''ባል እና ሚስት ከአንድ ባልዲ ይቀዳሉ"" ብሎ የተረተውም ከላይ ያልኩትን ሀሳብ ያወፍርልኛል:: ባልና ሚስት ከአንድ ባልዲ ይቀዳሉ ሲባል ሁለቱን አንድ አይነት ሀሳብ ያስባሉ ማለት ብቻ ሳይሆን: በአይን ተነጋግረው ይግባባሉ: በአይን ብቻ ፍቅር ይሰራሉ: የሚፋቀሩ ከሆነ ቢጣሉ እንኳን የትም ዞረው ይገናኛሉ የሚሉትንም ያጠቃልላል:: የትዳር አጋሩን ሀሳብና ፍላጎት የማይረዳ ካለ እርሱ ከትዳር አጋሩ ጋር በአንድ ባልዲ ውስጥ እንዳለ ውሀ አይደለም ማለት ነው::
በትዳር ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች ወይም ሰላማዊ ትዳር ላለመምራት እክል ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች የታወቁ ቢሆኑም ብዙ ጊዜ ልብ ብለን እነዛን ነገሮች ለማስተካከል ስለማንሄድ ችግሩ አፍጦ መጥቶ ጋብቻን እንደ ከርቸሌ (እስር ቤት) የምንቆጥር ብዙ ነን:: ከጭንቀት እና ፍርሀት: ረዥም ሰአት ከመስራት: ከድካም: የሰው ወሬ ከመስማት: ያለሆነ ነገር በአእምሮ ፈጥሮ ከማሰብ የተነሳ የትዳር አጋርን ጣል ጣል የማድረግ ነገር ይመጣል:: ""ረዥም ሰአት የሚሠራ: ፍርሀት እና ጭንቀት ያለበት እንዲሁም የሚደክመው ሰው ችግሩን ቀስ ብሎ ከማስረዳት ይልቅ ቁጣ ቁጣ ይለዋል::"" የሚሉት የስነ-ልቦና ባለሙያዎች ""ንግግሩ ሁሉ የፍቅርና ትህትህናን የተሞላ ሳይሆን የንቀትና በጣም የጮኸ ስለሚሆን የትዳር አጋርን ሊበጠብጥና ወደ አልተፈለገ ንትርክ ሊመራ ይችላል::"" ይላሉ:: እነዚህ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ለዚህ እንደመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርቡት ባልና ሚስት ረዥም ሰአት የሚፈጅ ሥራ መስራት እንደሌለባቸው ነው:: ሁለት ሙሉ ሰአት ሥራ የሚሠራ አንድ ወገን ለ16 ሰአታት ከሚስቱ ተለይቶ በሥራ ላይ ተወጥሮ ውሎ በ17ኛው ሰአት እቤቱ ሲገባ አልጋው ነው የሚናፍቀው ወይስ ከሚስቱ ጋር ቁጭ ብሎ የፍቅር ጨዋታ መጫወት?
አብዛኞቻችን በትዳር ውስጥ ችግሮች እንዴት እንደሚፈጠሩ በልምድም ልናውቀው ስለምንችል ወደ መፍትሄዎቹ ብናመራ የተሻለ ይሆናል::
ታደምጣታለህ ወይ?
የትዳር አጋርህ ላንተ ልክ እንደ ሴት አያትህ ናት ይላሉ የስነልቦና ባለሙያዎች:: አያቶች ለልጅ ልጆቻቸው እድሜያቸው በገፋ ቁጥር ብዙ ማውራትን እና ብዙ መምከርን ያበዛሉ:: ስላሳለፉት ነገርም በብዛት ያወራሉ:: አያቶች ዝም ብሎ ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጣቸውን እንደሚወዱት ሁሉ የትዳር አጋርህም እንደዚያው ናት:: ምንም ዝምተኛ ሚስት አገባው ብትልም ሚስት ከባሉዋ የምትደብቀው የላትምና ያሳለፈችውን ውሎ ስትነገርህ ማዳመጥ አለብህ:: ወሬው የሚያስጠላ ቢሆን እንኳ በአጽንኦት እየተከታተልክ መሆንን ለማረጋገጥ ''እህ"" ""አሀ"" ""ከዛስ?'' እያልክ በማዳመጥ ልታበረታታት ይገባል:: ከትንሽ ጀምሮ ሚስትህን የምታደምጣት ከሆነ ጸብ ቢፈጠር እንኳ የመደማመጡ ባህልን ስላዳበርክ በአጭሩ እሳትን ማብረድ ትችላለህ::
እርሷ ስትናደድ ምን ታደርጋለህ?
እርሷ ተናዳ በነገር ልትቆሰቁስህ ትችላለች:: ጮክ ብላ እየተናገረች ታቆስልሀለች:: በዚህ ወቅት አንተም እንደ እርሷ እሳት ትሆናለህ? መልስህ አዎ ከሆነ ተሳስተሀል:: አንዲት ሴት ልጅ ጮክ ብላ በንዴት ከተናገረች ""የጎደለኝ አለና ስማኝ"" እያለችህ መሆኑን ማስተዋል አለብህ:: የጎደለባትን ነገር ለማስተካከል መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ አብረሀት ብትጮህ እና ብትለፋልፍ: ቃላት ብትወራወር ትርፉ ራስን ማዋረድ ነው:: ቃላት በተወራወርክ ቁጥር የሚያደማ ቃል ትነጋገሩና ቁርሾ ማሳደር ይሆናል:: ነገርን ከመፍታት ይልቅም የባስ ትልቅ ጦርነት በቤትህ አወጅክ ማለት ነው:: ለዚህ ነው በተለመዶ ""ትዳሩን መምራት ያልቻለ ሰው ለሀላፊነት አይበቃም"" የሚባለው:: ስለዚህ ለማዳመጥ የፈጠንክ ለመልስ የዘገየህ ሁንላት::
ይባስ ብለህ እንደውም እርሷ በምትበሳጭበትና ጮክ ብላ በምትናገርበት ወቅት ንዴት ውስጥ ብትሆንም ዓይን ዓይኑዋን እና ከንፈር ከንፈሯን ብቻ ተመልከት ይላሉ የስነ-ልቦና ሊቆች:: እርሷ በንዴት ውስጥ ሆና አንተ ዓይን ዓይኑዋን የምትመለከታት ከሆነ ንዴቷ እየበረደ ከመሄዱም በላይ ያሳለፋችሁትን መልካም ጊዜ በዛች ቅጽበት ውስጥ አስታውሳ እርሷም ታጋሽ ባል አለኝ ብላ እንድትኮራብህ ታደርጋታለህ:: ትንሽ በረድ ካለች በሗላ ደግሞ ከንፈሯ አተኩእርህ በመመልከት ከአንገት በላይ ከእርሷ ጋር አንድ ለመሆን ፍላጎትህን አሳያት:: ለስለስ ያለ የከንፈር ለከንፈር መሳሳም ቁጣን አብርዶ እቤትህ ውስጥ ሰላምን እንደሚፈጥርልህ ሁልጊዜም አስተውል::
ስልክ ባታነሳስ?
አንተ ሥራ ቦታ ነህ እንበል:: እርሷ እቤት ውስጥ ነች ወይም ከቤት ውጭ ወጥታለች:: ባለቤትህ ናፍቃህ ወደ እርሷ ቴሌፎን ስትደውል የስልክ ጥሪ ባትመልስ ምን ታደርጋለህ? እንደ የስነልቦና ሊቆች አጠቋቆም ከ100 አስር የሚያህሉት እንኳ ሚስታቸው ቴሌፎን አለማንሳቷን በጥሩ ጎኑ አይመለከቱትም:: አብዛኛው ወንድ የሚያስብው ""ስልኩን ከሌላ ወንድ ጋር እያወራችበት ነው: ወይኔ በእኔ ላይ ደርባ ይዛብኛለች"" ብሎ ነው ወዲያው የሚያስበው:: ምናልባት በኔት ወርክ ምክንያት እየጠራ እርሷ ጋር ላይሰማ ይችላል: የቴሌፎን ባትሪ አልቆባት ይሆናል: ምን አልባት ስልክ ማውራት የማትችልበት ቦታ ይሆናል: ወይም ሥራ ቦታ ውጥረት ውስጥ ትሆናለች ብሎ የሚያስብ ከስንት አንድ ነው:: አንተም ለአጋርህ ስትደውል ስልክ የማትመልስ ከሆነ ወዲያውኑ በመጥፎ ጎኑ የምትመለከተው ከሆነ አመለካከትህ መልካም ስላለሆነ ለመቀየር ሞክር::
እድሜ ለቴክኖሎጂ ""የድምጽ መልእክት ማስተላለፊያ"" (Voice massage) ተፈጥሮልናልና ይህን ተጠቀምበት:: ስልኩ ጠርቶ የማይነሳ ከሆነ ""የእኔ ፍቅር... (እንደዚህ ያሉትን ቃላት በጸብም ሆነ በፍቅር ጊዜ አትርሳ) የእኔ ፍቅር ናፍቀሺኝ ደውዬልሽ ነበር:: ሆኖም ስልክ ማናገር በማትችይበት ሁኔታ ውስጥ እንዳለሽ እገምታለው:: ስለዚህ በሗላ እንደዋወላለን:: እወድሻለው"" የሚል አይነት ትህትናንና ፍቅርን የተላበስ መልእክት አስቀምጥላት:: እንደዚህ ያሉት መልእክቶች ሚስትህ አንተ እንደምትጠረጥረው ከሌላ ወንድ ጋር እንኳ ሄዳ ቢሆን ትህትህናን እና አስተዋይነትህን አይታ ራሷን ትሰበስባለች:: ""ባለቤቴ ራሱን ስለሚያምን እኮ ነው እኔን የሚያምነኝ"" ብላ እንድታስብ ታደርጋታለህ:: አለበለዚያ ግን ለምን ስልክ አታነሺም እያልክ የምትጮህ ከሆነ: የስልክ ጥሪ አለመመለሱዋንም በመጥፎ መንገድ የምታየው ከሆነ ""ራሱን የማያምን ሰው ሰውን አያምንም"" የሚለውን ብሒል እውን እንዲሆን ታደርጋለህ::
የፍቅረኛነት ዘመንን የሚያስታውስ ትዝታን ትፈጥራለህ ወይ?
በፍቅረኛንት ዘመንህ ታሳያት የነበረህን የሰጪነት (የለጋስነት) ባህርይ ትዳር ውስጥ የሚከለከል እንዳይመስልህ:: ትዳር እስር ቤት አይደለም:: እንደውም በፍቅረኛንት ዘመን ከነበርክበት ጊዜ በበለጠ አሁን ከአጋርህ ጋር በነጻነት የምትገናኙበት ጊዜ ነውና ይበልጥ ለጋስነትህን ማሳደግ ይኖርብሀል:: ምንም እንኳ በፍልስፍና ዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች ""ሴቶች ፍላጎታቸውን አይደለም ወንድ ራሳቸውም አያውቁትም"" ቢሉም እንደፍላጎቷ ሁንላት:: በመንገድ ላይ ስትሄዱ የልብስ መሸጫ ሱቅ አጠገብ ስታልፉ ""ይህ ልብስ ያምራል"" ብትልህ እንድትገዛላት ፍላጎቷን እያሳየችህ ነው:: ገንዘብ ባይኖርህ እንኳ አብረሀት ልብሱን አድንቅ እንጂ ""አንቺ ደግሞ ሁሉም ያምርሻል"" ብለህ ፍላጎቷን ኩም አታድርገው:: ዛሬ ባትገዛላት ሌላ ጊዜ እንደምትገዛላት በፍቅር ቃላት ንገራት:: ይሄኔ ልብሱን የለበሰችው ያህል ከአፍህ የወጣው የትህትና ቃል ሰውነቷን ይሞላዋል::
ልክ እንደዚሁ ሁሉ በትዳር ውስጥ አብረህ በምትኖርበት ወቅት በተቻለህ መጠን የተዋወቃችሁበትን ቀን ሁልጊዜ አንተ አስተዋሽ ሆነህ አነሰም በዛም ስጦታ ስጣት:: ሴቶች እንደዚህ የሚያደርግን ወንድ እንደ ንጉሥ የመመልከት ባህርይ ስላላቸው በተቻለህ መጠን እርሷን ድንገት የሚያስደስቱ (surprise) ነገሮችን ለማድረግ ሞክር:: በተለይ አመታዊ የትውውቅ በዓላችሁን ስታከብሩ ድሮ በፍቅረኛነት ዘመን ትዝናኑበት የነበረው ሆቴል ይዘሀት ሄደህ ራት ጋብዛት:: እዛም እደሩ:: ይህን ካደረግክ ቤቷ እንዲናፍቃት ከማደረግህ በላይ የፍቅረኛነት ጣፋጭ ጊዜያችሁን በትዝታ መነጽር ዞር ብላ እንድታስታውስ ታደርጋታለህ:: ይህ ሲባል ግን ራት ይዘሀት የምትወጣው የግድ በዓላትን መጠበቅ የለብህም:: አብሮ ለሚኖር ሰው ሁልጊዜ በዓል ነው::ð

ሃበሻ በሱዳን

ሱዳን ላይ ውሃ ሲጠማህ የምትጠጣው ከዚህ እንስራ ቀድተህ ነው.... ምናልባት ትል እ ና ትናንሽ እንቁራሪቶች ሊገኙበት ቢችሉም ውሃ ስለሚጠማህ ብቻ ዝም ብለህ መጠጣት ነው.....

ሐበሻ በሱዳን - ከሔኖክ ዓለማየሁ




ሰው በተለያየ አጋጣሚ ይሰደዳል:: እኔ ስደትን በሁለት አይነት እከፍለዋለሁ:: አንደኛው የቅንጦት ስደት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአስገዳጅ ሁኔታዎች የሚከሰት ስደት ነው :: የቅንጦት ስደት በኢትዮጵያ ሀገሩ መኖር እየቻለ የምእራብያውያን ናፋቂ የሆነው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ብዙሀኖቻችንን የሚወክል ይመስለኛል:: ጥቅምት 22/1997 አ .ም ነበር ከኢትዮጵያ የወጣሁት :: በዚህ ቀን ከሀገሬ ከመውጣቴ በፊት አንድ ነገር በጣም አስገርሞኛል:: እሱም የኢትዮጵያን ደህንነት አሰራር የታዘብኩበት ነው:: ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በጣም ይፈለግ ስለነበር በኤርፖርትም በድንበርም ከሀገር እንዳይወጣ ስሙ ተላልፎ ነበር:: ለጊዜው ስሙን ወደማላውቀው ሀገር አንድ አውሮፕላን ይነሳል:: በዚህ አውሮፕላን ላይ እስከዳር ነጋ የምትባል ሴት ተሳፍራለች:: አውሮፕላኑ እንደተነሳ አየር ላይ 20 ደቂቃ እንደፈጀ ተመልሶ እንዲያርፍ ተደረገ:: የኢትዮጵያ ደህንነቶች ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አመለጠን ብለው ተራወጡ:: መጨረሻ ላይ አውሮፕላኑን አስመልሰው ሲፈትሹ የተገኘችው ወ/ሮ እስከዳር ነጋ ናት:: እንግዲህ ይታያችሁ ወንድና ሴት መለየት የማይችሉ ስዎችን :: አውሮፕላኑን ደግመው ከማሳረፍ ከአየር መንገዱ የበረራ ሪፖርት መመዝገቢያ ላይ የሴትየዋን ማንነት ማረጋገጥ ይሻላል ወይስ?....
በዚህ የተነሳ የመተማን ድንበር አቋርጬ ወደ ሱዳን ለመግባት ምንም ፍራቻ አላደረብኝም :: እንደነ ነዋይ ደበበ ''በገዳሪፍ ካርቱም'' የሚለውን ዘፈን እየዘፈንኩ ገዳሪፍን አልፌ ካርቱም ገባሁ::
ተወርቶ የማያልቅላት ዴም
ካርቱምና የሀበሻ ስም ከተነሳ 'ዴም ' አትቀርም :: ዴም ዛሬ አውሮፓ ውስጥ ከሚገኙ ሊቢያን ለረገጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሕይወታቸው አንድ ክፍል ናት ብል አላጋነንኩም :: ለምሳሌ እስኪ ዴም አዝመራን ; እማማ (ነብሳቸውን ይማር ከሞቱ አመት ሊሞላቸው ነው) የማያውቅ ማነው? በተለይ እማማ ቤት ግድግዳ ላይ ከተጻፉ የግድግዳ ላይ ጽሁፎች በተለይ የጨርቆስ አካባቢ ልጆች የሳቸው ድንበኛ ነበሩ :: እማማ ሥራቸው አንድ ትልቅ ቤት ተከራይተው ''ኬሻ በጠረባ '' ሊባል በሚችል አተኛኘት በቀን 2 የሱዳን ሊራ እየተቀበሉ የሚያሳድሩ ሴት ናቸው:: ካርቱም ላይ በሙቀት የተነሳ ከቤት ውጭ ስለሚተኛ ለሳቸው ገበያ በጣም ተስማሚ ነው:: ምክንያቱም ያቺን የሲባጎ አልጋ ማታ ማታ እየዘረጉ ያሳድራሉ:: በጣም የሚገርመው እማማ ቤት በአንድ ለሊት እስከ 60 ሊደርስ የሚችል ሰው ማደሩ ነው:: ''ትንሽ ጨቅጫቃ ናት ; ግን የዋህ ናት '' የሚል ስም ያላት አዝመራ ቤት ውስጥ ከተለጠፉ ጥቅሶች መካከል ይህን ጽፌ ነበር:-

“የአባትህን ገዳይ አትበቀለው ሱዳን ካርቱም አምጥተህ ያለ ሀዋላ ጣለው”

ይህ ጥቅስ የሚያሳየው የካርቱም የሀበሻ ኑሮ ምነኛ አስቀያሚ እንደሆነ ያሳያል:: ከምግብ ውስጥ ርካሹ ፉል ነው ሱዳን ውስጥ ይህ የሚጠፋበት ጊዜ ብዙ ነው:: ለብዙዎቻችን ፉል እንኳ መግዢያ የሱዳን 50 ሳንቲም (ጅኔ) ይጠፋል:: እናም ይህን ለማሳየት ነው ጥቅሱ የተጻፈው:: ካርቱም ላይ እጅግ ታዋቂ ከሆኑ ሰዎች ሁለቱን ከጠቀስኩ ከዴም ጀምሮ ; ከሰሀፋ ዘለጥ እስከ ጅሬፍ; ከአባሁማማ እስከ አንዱርማን እና ሌሎችም ሰፈሮች የቃረምኳቸውን ታሪኮች ተራ በተራ ላስነበብ ::
ሣራ
ሣራ የብዙ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች መጠሪያ ስም ነው ካርቱም ላይ:: አንዷን ሴት አግኝተህ ማነው ስምሽ ብትላት ሣራ ትልሀለች:: ለምንድን ነው ዋና ስምሽን የምትቀይሪው ስትላት 'ለአጠራር እንዲመች' የሚል ተልካሻ ምክንያት ያቀርቡልሀል:: ዋናው ምክንያታቸው ራሳቸውን ለመደበቅ እንደሆነ የታወቀ ነው :: ራሳቸውን ከማን ይደብቃሉ ? እንዳትሉኝ :: ዛሬ ሳራ የሆነቸው ሴት ነገ 'ሀያት ' ከነገ ወዲያ 'ኢማን ' ይሆኑላችኍል :: ለምን ስማቸውን ይቀይራሉ? በቀጣይ ዘገባዎቼ መልስ ታገኛላችሁ :: በዚህ የተነሳ የሱዳን ሰዎች ኢትዮጵያዊ ሴት ሁሉ ሣራ ይመስላቸዋል:: አንዲትን ኢትዮጵያዊትን ሴት መንገድ ላይ ሲጣሩ እንኳ ሣራ ነው የሚሉት በብዛት::
ተክለሀይማኖት አካባቢ እንደተወልደች የምትናገረው ሣራ የሱዳንን ምድር ከረገጠች 2 አመት ሊሞላት የቀናት እድሜ ብቻ ነበር የቀሯት :: ለምን ወደ ሱዳን መጣሽ? ነበር ያልኳት - የምትሰራበት የላስቲክ ሻይ መሸጫ ቤት ውስጥ ገብቼ ቁጭ ካልኩና ብዙ ከእርሷ ጋር ከተግባባው በኍላ:: 'ከዚህ ቀደም በሌላ አረብ ሀገር ነበር የምኖረው :: የአረብ ገረድ መሆን መረረኝ:: እስኪ የአውሮፓን ሕይወት ልይ ብዬ ወደ ሱዳን መጣሁ' ስትል ትረካዋን የጀመረችው ሳራ 'ወሬውን የሰማሁት አዲስ አበባ እያለሁ ነው :: ብዙ ስዎች ሱዳንን አቋርጠው በሊቢያ በኩል ወደ ጣሊያን ይገባል ሲሉ ሰምቼ መጣሁ .: ከእኔ ጋር የመጣች ልጅ አሁን ሊቢያ ትገኛለች እኔ እድሌ ሆኖ ሱዳን ቀረሁ ' አለችን በቁጭት:: ለሳራ ሊቢያ መግባት ትልቅ ስኬት ነው:: ሊቢያ ምን ስቃይ ይኑር ; ይሙቅ ይድላ የምታውቀው የላትም:: ብቻ እሷ ሰዎች ያንን መንገድ ተጠቅመው ጣሊያን ስለሚገቡ ብቻ ሊቢያ የስኬቷ ምንጭ ነው::
ጥያቄዬ አላቋረጠም 'ለምን አልሄድሽም ታዲያ ?' አልኳት :: እምባዋ በአይኖቿ ጎን ብቅ ማለት ጀመሩ :: ታሪኬ ብዙ ነው ተወኝ አለችና እንደመመናቀርም ብላ ወደ ጓዳ ገባች:: በጣም ጓጓሁ:: ልጅቷ አንድ የተደበቀ ምስጢር አላት አልኩ:: ታዲያ ይህን ለማግኘት የግድ እርሷን መቅረብ ይገባኛልና ቀረብኳት:: ከብዙ ውትወታ በኍላ ልጅቷን 'አማራት' (street) 41 የሚባለው ሰፈር የሚገኘው ጋልፍ መዝናኛ ቀጠርኳት:: ሱዳን ላይ በተለይ ሴት ልጅ ጋር ቀጠሮ የምትይዘው እሑድ (አሀድ) ወይም ጁምአ (አርብ) ነው:: እነዚህ ሁለት ቀኖች ብዙ ኢትዮጵያዊያን ኢጃዛ (እረፍት ) የሚወጡበት ቀን ነው::
...ለምን ቀጠሮውን አረፈድሽ አልኳት ብዙ እንዳስጠበቀችኝ ለማስገንዘብ :: 'ሴትየዋ ጨቅጫቃ ናት :: ቶሎ አትለቀኝም:: አሁንም አኩርፋ ነው የመጣሁት:: እኔ ከቤት ስወጣ አትወድም::' የትኛዋ ሴትዮ ብዬ ሳልጠይቃት የምትሰራበት በላስቲክና በሸምበቆ የተወጠረው ሻይ ቤት የሌላ ሀበሻ ሴት ንብረት እንደሆነና እሷ በቀን 10 የሱዳን ዲናር እየተከፈላት እንደምትሰራ ነገረችኝ:: 'አየህ ሱዳኖች ወንዶቹ የኛን ሴቶች ይፈልጋሉ:: የኛን ሴቶች ለማየት ሲፈልጉ ወደሻይ ቤታችን ይመጣሉ:: ሻይ ፍለጋ ሳይሆን እኛን ::' የምትለው ሳራ ወደ ሻይ ሥራ ለምን እንደገባች ስታስረዳ:: ታሪኩ ብዙ ነው ትላለች ::
በወር 150 ዶላር ደመወዝ ይከፍልሻል ብለው ወደሱዳን ያመጡዋት አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ደላሎች ናቸው:: ለሱዳን 5 ሺህ ብር ክፍላ መምጣቷ ሳያንስ በሱዳን አሰሪዎቿ የደረሰባት ነገር እጅግ ያሳዝናል:- 'አንድ ቀን ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ እንደወትሮዬ ከሁሉም ቀድሜ ተነስቼ ቤቱን የማጸዳው እኔ ስለነበርኩ አይኔን ሳልገልጥ ስወጣ ቤቱ ደጃፍ ላይ ድመት ታርዶ አንገቱና ሰውነቱ ተለያይቶ ተጥሎ አገኘሁ ....'
''የታረደውን ድመት እንዳየሁ አዞሮኝ ወደቅኩ:: ከዛ በኍላ ራሴን ያወቅኩት ከአንድ ቀን በኍላ ነው:: የሴትዮዬ (ማዳሟን ነው) ባል ከአጠገቤ ተቀምጦ ነበር :: ከዛም የሆነውን ሁሉ ጠየቅኩት :: ድመት አርደው በር ላይ እንዲጥሉ ያደረጋቸው እምነታቸው እንደሆነ ነገረኝ '' የምትለው ሳራ ከዛ በኍላ ራሷም የእምነቱ ተከታይ በመድሐኒት እንዳደረጓት እምባዋ እየወረደ ነገረችኝ::
ሱዳን በሳይንስ የተረጋገጠ መረጃ ባላገኝም እንደሚወራው ከሕንድ ቀጥሎ ሁለተኛዋ የባድ ስፕሪት (ጠንቋይ) ሀገር ናት:: ሙአሰላት (አውቶቡስ) ውስጥ እየሄድክ ከአጠገብህ ጀለቢያ ያደረገ ቁመተ ረዥም ሱዳኒ ማግኘት የአፈር ያህል ነው:: ይህን ሱዳን ትንሽ እንዳወራህው ስለ ግል ህይወቱ ብትጠይቀው ጥንቆላ እንዳለበት ካለምንም ማፈር ይነግርሀል::
አንድ ቀን የሀበሻ ምግብ ቤት ውስጥ ቁጭ ብዬ በምሰማት ጥቂት አረብኛ ቋንቋ አንዱ ጠብደል ሱዳን ለኛ ሴት ክንዱ ላይ በቁልፍ የታሰረ ቀበቶ ያሳያታል:: እሱም ይህን እያሳያት የሚነግራት ነገር ያሰረው በቁልፍ የታሰረው ቀበቶ ማንኛዋም ያናገራት ሴት እንድታፈቅረው እንደሚያደርግ እና ጥይት ቢተኮስበት እንኳን ይህ እንደ ሚከላከልለት ሲነግራት ስምቻለሁ:: ልክ እንደዚሁ ሁሉ ሱዳን ውስጥ ስለ ጥንቆላ ማውራት በጣም አይቸግርም::
ይህን ስል ሱዳን ያሉ የእኛም ሰዎች ጤነኛ ናቸው ማለት አይደለም:: አብዛኞቹ ቀን ቀን ካርቱም መድሐኒአለም ማታ ማታ ሱቀል ዴም ያለው ጠንቋይ ቤት አይጠፉም:: ብዙሀኑን የሀበሻ የላስቲክ ቤት ሻይ ቤቶች ስትጎበኙም መሬቱን ስታዩ ጥቁር አዝሙድ ተንስንሶ ታያላችሁ :: ጥቁር አዝሙድ እና ጥንቆላ ምን አገናኘው ብዬ ጠይቄ ግን ምላሽ ማግኘት አልቻልኩም :: **** **** ***** እምባሽን አቁሚ ብዬ እያባበልኩ ጨዋታዋን እንድተቀጥልልኝ አደረግኩ ::
ሱዳንና ሱዳናውያንን እየቃኘን ነው:: የኛ ሰው በሱዳን ምን እንደሚመስል እያየን ነው:: አብዛኞቹ በባእድ አምልኮ ወደውም ይሁን ሳይወዱ እንዴት እንደሚገቡ ለማሳየት እየሞከርኩ ነው:: ሳራ በታረደ ድመት ዞሮባት የባእድ እምነቱን መከተል ጀምራለች:: ''ከወደቅኩበት እንደተነሳው የተነገረኝ ነገር ቢኖር ያዳነኝ አምላክ ድመቱ የታረደለት እንደሆነ ነበር '' ያለችኝ ሳራ የአሰሪዋ እናት በካርቱም ታዋቂ ጠንቋይ እንደሆኑ አስረግጣ ነገረችኝ::
ከዛስ? 'ከዛማ ወደ አባይ ወንዝ (ካርቱምን የሚያቋርጠው) መሄድ ጀመርኩ :: አንድ ምሽት ሴትዮዬ ልጃቸው እና እኔ ሆነን ወደ ባህር ሄድን :: ከሌሊቱ 6 ሰአት አካባቢ ነው:: ባህሩ ከምሰራበት አንዱርማን የ 30 ደቂቃ መንገድ ቢኖረው ነው:: እዛ ሄደን ከመኪናው እንደወረድን ሴትዮዬ ቀድማ ወደ ባህሩ ተጠጋች :: ከዛም መኪናው ውስጥ ከያዝነው የተቀጣጠለ ክሰል ጋር እጣን ነስንሳ ወደ ባህሩ ጋር ተጠጋች :: የሚሆነው ነገር ሁሉ በጣም እያስገረመኝ መጣ:: ሴትዬዋ ተንበርክካ እያለቀሰች አንዳንዴም እያጓራች እጣኑን ወደባህሩ ይዛው ትንሽ ገባ አለች:: የዛን ጊዜ ከወንዙ ውስጥ ያሉት አሶች ወደላይ እየዘለሉ እየወጡ ሲገቡ ተመለከትኩ :: በጣም ደነገጥኩ :: አጠገቤ ያለው ልጃቸውና ሚስቱ ተንበርከክው ማጉዋራት ጀመሩ:: ራሴን ስቼ ወደቅኩ'' በሚል ታሪኳን ተረከች:: ተመስጬ እያዳመጥኳት ነው::
''ከሁለት ቀን በኍላ ነው የነቃሁት:: ሴትዮዬ ስነቃ ወደ እኔ መጥታ ከአሁን በኍላ እኔ ቤት ሥራ አትሠሪም:: የባህሩና የድመቱ አምላክ ላንቺ የሚሆንሽን ሰው መርጦልሻል'' ብላ ከአንድ ሀብታም የዚህ ባእድ አምልኮ ተከታይ ሱዳን እንዳጋባቻትና ከዚህ ሰው ጋር አብራ ለጥቂት ጊዜ እንደኖረች ነገረችኝ:: ከዛም ይህ ሱዳን እሷን የሚፈልገውን ያህል ከተጫወተባት በኍላ ለሥራ ቤቱ ከተቀጠረች ሌላ ኢትዮጵያዊት ጋር ግንኙነት ጀምሮ በእኩለ ሌሊት ከእቤት እንዳስወጣት ጨምራ እያለቀሰች ነገረችኝ::
የምትነግረኝ ነገር ስሜቴን እየጎዳው ነው :: በዛ ላይ የምታነባው እምባ በጣም ልብን ይነካል :: ሰው መሆንንና መፈጠርን ሁሉ ያስመርራል :: መጨረሻዋ ሻይ ቤት መሥራት ይሁን እንጂ እዚህ ላይ እንዴት እንደደረሰች ጠየቅኳት ::
''አንዱርማን የሚኖሩ ሀበሾች አብዛኞቹ የተጣባቸው ባእድ አምልኮ ስላለ እነሱ ምንም ይረዱኛል ብዬ ሳላስብ ወደ ካርቱም መጥቼ ዴም ያሉ ሀበሾች ይረዱኝ ዘንድ መጣሁ :: እዛ እንደመጣሁ ወደ ሊቢያ የሚሄዱ የአዲስ አበባ ልጆች አገኘሁ :: ስምሽ ማነው ሲሉኝ ቤቲ አልኳቸው :: ስሜን ለሦስተኛ ጊዜ መቀየሬ ነው:: የደረሰብኝን ሳልነግራቸው አዲስ መጤ እንደሆንኩና ሱዳንን ምንም እንደማላውቅ ብሎም ገንዘብ እንደሌለኝ እያለቀስኩ ነገርኳቸው :: አዘኑና እኛም ቤት የለንም :: ቢሆንም በቀን ሁለት ብር እየከፈልን የምንኖረው አዝመ ራ ቤት ነው:: ሥራ እስከምትጀምሪ ድረስ እኛ የምንበላ ውን ፉል እየበላሽ ትኖሪያለሽ; የአልጋም እንከፍላለን አሉ::
''ከእነሱ ጋር ለ3 ቀናት ያህል እንደተቀመጥኩ 'ማዳም ቤት' (የሰው ቤት ሥራ ማለት ነው ) ሥራ አገኘሁ:: ቢቸግረኝም አልሰራም አልኩ:: ልጆቹ ለምን አሉ? ሥራ አትወጂም ማለት ነው ብለው የሚያስከፋ ቃላትን ሰነዘሩብኝ:: እኔ ማዳም ቤት ሥራ አልሰራም ያልኩት የደረሰብኝ አሰቃቂ አደጋ እንዲደገም ስለማልፈልግ እንጂ ለሌላ አልነበረም :: ቢሆንም ልጆቹ ጥሩ ነገር ቢያደርጉልኝም ስሜቴ ቶሎ ስለሚጎዳ ትቼ ወጥቼ መንገድ ላይ ስሄድ አንድ ሀበሻ አግኝቶኝ እኚህ ሴትዮ ቤት ሥራ አስገባኝ '' አለች የቀድሞዋ ሣራ የአሁኗ ቤቲ::
በጣም የሚያሳዝነው የቤቲ ሕይወት ከድጡ ወደማጡ ነው :: ከሱዳን ቤት የወገኔ ቤት ይሻለኛል ብትልም እኚህም ሴት ያው ናቸው :: ለምሳሌ አንድ ቀን እሳቸው ቤት ሻይ ልጠጣ ከካርቱም ጓደኞቼ ጋር ገብቼ ሳላውቅ አንድ ጥግ ስር የጎዘጎዙትን ሳር : የበተኑትን ጥቁር አዝሙድና ፈንዲሻ ረግጭባቸው ሁለተኛ እዚህ ቤት እንዳትደርስ ብለው አባረውኛል :: ግን ዝንጉ ስለሆኑ በሌላ ቀን ስሄድ አስገብተውኛል ::
''በቀን 5 ጊዜ ለአሮጊቷ ቡና ማፍላት አለብኝ:: ጠዋት የላስቲክ ቤቱን ሻይቤት ከመክፈቴ በፊት እግሯን የተቆረጠች እርግብ አለቻቸው:: ለእርሷ ስንዴ መበተን አለብኝ:: ያንን ባላደረግኩ ቀን ገበያ የለም:: ቤቱ ጭር ብሎ ይውላል:: ታዲያ ማታ ሂሳብ ስንሰራ ሂሳቡ ሲያንስባቸው አሮጊቷ አያስቀምጡኝም : ለምን ለእርግቧ ስንዴ አልበተንሽም ; ለምን ጥቁር አዝሙድ መሬቱ ላይ አልነሰነስሽም በሚል ብዙ ውርጂብኝ ያወርዱብኛል '' ብላኛለች:: ያው የእኔ ሥራ ከማዳመጥ በቀር መጠየቅ ነውና ለምን ታዲያ ቤቱን ለቀሽላቸው አትወጪም ስላት ''ምን እንዳዞሩብኝ አላውቅም አንዲትም ቀን ቤቱን ስለመልቀቅ አላስብም :: የምፈልገውን ቢዝነስ አገኛለሁ'' አለችኝ :: ቢዝነስ በካርቱም ሌላ ትርጉም አላት :: አብዛኞቹ ሻይ ቤት የሚሰሩ ሴቶቻችን ቢዝነስ አላቸው:: ምን? (ሐበሻ በሱዳን..... በቀጣዩ እትም ይቀጥላል።)

ካንቺ በዲት ኤ.አይቪ እንዳለበት እያወቀ ቢያገባሽ ምን ታደርጊያለሽ?


ወደ ታሪኩ ከመግባታችን በፊት ቆም ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፤ ዛሬ አብሮሽ በትዳር ያለ ጓደኛሽ ወይም በወሲብ የምታውቂው እጮኛሽ የኤች አይቪ ቫይረስ በደሙ እንዳለ እያወቀ ካንቺ ጋር አልጋ ላይ ቢወድቅና አንቺም ትዳር ላይ ከገባችሁ በኋላ ይሕንን ብታውቂ ምን ታደርጊያለሽ? ያንቺን ውሳኔ እወቂና ምህረት አስቻለው ያጠናቀረውን እውነተኛ ታሪክ ተከታተይ።
ባህር ዳር ከተማ ውስጥ በግ ተራ ተብሎ የሚጠራ አካባቢ ነው፡፡ ምሽት አሥራ ሁለት ሠዓት ገደማ ወደ አንድ ደሳሳ ቤት ጠጋ ብለን በር አንኳኳን ምንም ምላሽ አላገኘንም፡፡ ደግመን ስናንኳኳ ግቡ የሚል የወንድ ድምፅ ከወደ ውስጥ ሠማን፡፡ የቆርቆሮውን በር ገፋ አድርገን ስንገባ ፊት ለፊት በግምት እድሜው ሦስት ዓመት የሚሆን ህፃን ፊት ለፊት ወንበር ላይ፣ አይናቸው ላይ መሀረብ ጣል አድርገው ጠባብ አልጋ ላይ ተንጋለው የተገኙ አዛውንት ተመለከትን፡፡ አዛውንቱ ህፃኑን እናቱን እንዲጠራ አዘዙት፡፡
ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገችው ወ/ሮ ተወልዳ ያደገችው አዲስ ዘመን የሚባል አካባቢ እንደሆነ፤ ትዳር የመሠረተችውም (አዛውንቱን ያገባችው) በቤተሰብ በኩል እንደሆነ ገልፃልናለች፡፡ ጋብቻ የመሠረቱት 1986 ዓ.ም. ላይ ነበር፤ በዚያ ወቅት ባለቤቷ በጦር ሠራዊት ውስጥ ያገለግሉ እንደነበርም አስታውሳለች፡፡
ሦስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ የመጀመሪያው የአሥራ አራት፣ ሁለተኛዋ የዘጠኝ ዓመት፣ በር ከፍተን ስንገባ የተመለከትነው ህፃን ደግሞ የመጨረሻ ልጃቸው ሲሆን ሦስት ዓመቱ ነው፡፡ ከጡረታ በሚገኝ ገንዘብና አትክልት እየቸረቸረች ወይዘሮዋ ቤተሰባቸውን ታስተዳድራለች ልጆቿንም ታስተምራለች፡፡
“ባለቤቴ በተደጋጋሚ ይታመም ነበር፡፡ ሁለተኛዋ ልጄም ዘወትር ትታመም ስለነበር ጥርጣሬ አደረብኝ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ባለቤቴ ከጦር ሠራዊት ተሰናበተ፡፡ የባለቤቴም የዘጠኝ ዓመት ልጄም ህመም ቀን ከቀን እየበረታ መጣ፡፡ ባለቤቴ ይጠጣል በዚህም ዘወትር እንጋጫለን፡፡ ትዳራችን በብዙ መልኩ ችግር ውስጥ ገባ” ብላለች፡፡
ህፃን ልጇ በጣም መታመም ስለጀመረች ወደ ሆስፒታል መሄድ የግድ ሆነ፡፡ ለህፃኗ ምርመራ ከተደረገላት በኋላ የህፃኗ እናት መሆኗን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንድታመጣና እሷም የኤች.አይ.ቪ ምርመራ እንድታደርግ እንደተነገራት አስታውሳለች፡፡ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በህፃኗም በእሷም ደም ውስጥ መኖሩ ተነገራት፡፡ ይህን ካወቀች በኋላ ትዳራቸው መፍረስ እንዳለበት በማመን ባለቤቷን እንዲፋቱ ጠይቃቸዋለች፡፡ ባለቤቷ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ፍርድ ቤት በማመልከት ፍቺ ጠይቃለች፡፡
ጉዳያቸው በመታየት ላይ እያለ ባለቤቷና ሌሎቹ ልጆቿ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ አድርገው እነሱም ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩ ሊታወቅ ችሏል፡፡ ይህ ደግሞ የወይዘሮዋን ቁጣ አባባሰው፡፡ “የልጃገረድ ባለቤቴ ነው፡፡ ከተጋባንም ወዲያ እኔ የማውቀው ነገር አልነበረኝም፡፡ እሱ ግን ስለህመሙ እያወቀ እንድንጋባ፤ ከዚያም እነዚህን ልጆች እንድንወልድ ማድረጉ በጣም አስቆጣኝ፡፡ በትዳር በቆየንባቸው ጊዜያት ሁሉ አንድም ቀን ምንም ብሎ አያውቅም” ትላለች፡፡
ወይዘሮዋ እንደምትለው፣ ቀደም ሲል በተለይም ገጠር እያለች ስለ ኤች.አይ.ቪ ብዙም የምታውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ባለቤቷና ህፃን ልጅዋ በተደጋጋሚ ይታመሙ ስለነበር ይህም ጥርጣሬ ይፈጥርባት የነበረ ቢሆንም የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በእሷና በባለቤቷ እንዲሁም በሦስት ልጆቿ ደም ውስጥ መገኘቱን መቀበል በጣም ፈታኝ ሆኖባት ነበር፡፡
ባለቤቷ፣ እሷና ሁለተኛ ልጇ ቫይረሱ በደማቸው መኖሩ እንደታወቀ ወዲያው ፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት ጀምረዋል፡፡ “እያወቀ እኔን እንዳገባኝና እነዚህ ልጆችም እንዲፈጠሩ አደረገ ብዬ ባለቤቴን
ሠላም አሳጣሁት፡፡ ቤት ውስጥ ሠላም ጠፋ፡፡ ባለቤቴም ከቤት ወጥቶ ሔዶ ነበር፡፡ እኔም በአንድ በኩል ህመምና ድህነት፤ በሌላ በኩል ብስጭት አእምሮዬን እንድስት አደረገኝ፡፡ ጉዳያችንን ፍርድ ቤት እየተመለከተው እያለ እኔም እየተረጋጋሁ መጣሁ፡፡ ከባለቤቴ ጋር ተለያይቼ የማገኘው የተሻለ ነገር የለም፡፡ ምን አልባትም ህይወት ሊከብደኝ ይችላል ብዬ አሰብኩኝ” በማለት ትዳሯን የማፍረስ ሃሳቧን ቀይራ በይቅርታ ከባለቤቷ ጋር ለመኖር መወሰኗን ነገረችን፡፡
ህመም በርትቶባት በተለያዩ ጊዜአት ተኝታ ነበር፡፡ ባለቤቷም በተደጋጋሚ ይታመማሉ፡፡ ከሁሉም በይበልጥ የምትታመመው ግን ህፃን ልጇ ነች፡፡ ጐረቤቶች በተለያየ አጋጣሚ ሽንት ቤት እንዳትጠቀም በማድረግና በለሎች ነገሮች አግልለዋት ነበር፡፡ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ግን ጐረቤቶቿ ከማግለል ይልቅ ሊያቀርቧት እንደሚፈልጉ፤ እሷ ግን ያለፈውን ትታ በይቅርታ እንደቀድሞ ከጐረቤቶቿ ጋር መቀራረብ አለመቻሏን በሀዘኔታ ገልፃልናለች፡፡
“ተመርምረን ራሳችንን ካወቅን ሁለት ዓመት ሆነን፡፡ በጣም አስቸጋሪ የሆነብኝ የሴቷ ልጄ ሁኔታ ነው፡፡ ዘጠኝ ዓመቷ ነው ግን ዘወትር ስለምትታመም ሠውነቷ ድቅቅ ያለ ነው” በማለት የሦስት ዓመቱን የመጨረሻ ልጇን ጭንቅላት በመዳሰስ “እሱን ነው የምታክለው” አለችን፡፡ “በቂ ምግብ ስለማታገኝም እንደሆነ አላውቅም መድሀኒቱን አልቻለችውም፡፡ ሁለት ጊዜ አስቀይሬላታለሁ፡፡ መድኃኒት የምትወስድበትን ሠዓት ለይታ ስለምታውቅ በዚያ ሠዓት ወደ መንደር ሔዳ ትጠፋብኛለች፡፡ የዋጠች መስላ ትተፋዋለች፡፡ እሷን ለመቆጣጠር ብዬ እኔም እሷም መድኃኒት የምንወስድበት ሠዓት አንድ ዓይነት አደረግኩት”
የመጀመሪያ ልጇ አሥራ አራት ዓመቱ ቢሆንም ስለ እናትና አባቱም ሆነ ስለታናሽ እህቱ ህመም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ስለራሱ ውጤትም አልተነገረውም፡፡ ፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት የምትወስደው ህፃን ግን ሁሌም መድኃኒት ውሰጂ ስትባል ለምን እያለች ትጠይቃለች፣ ላለመውሰድም ትታገላለች፡፡ð

አፍሪቃውያን እጃቸውን ወደ ባራክ ኦባማ ይዘረጋሉ



በአፍሪካ ሕብረት መዲና አዲስ አበባ እና በሌሎች ትላልቅ ከተሞች ''ኦባማ ቅዱስ ገብርኤል ይከተልህ'' ''ይቻላል"" እና የተለያዩ መፈክሮች ያሉበት የኦባማን ምስል የያዙ ቲሸርቶች ከምርጫው በፊት ገበያውን ሲመሩት ነበር:: እያንዳንዱ ሕዝብ የአሜሪካንን ምርጫ በአጽንኦት ሲከታተል የነበረ ሲሆን በአዲስ አበባ ሰፊ ተመልካች ያላቸው አልጀዚራ እና ሲኤንኤን የቲቪ ቻናሎች ሕዝባችንን በመረጃ ቀልበውታል:: ''ኦባማ የአፍሪካውያን ተስፋ"" የሚሉት አፍሪካውያን ከምርጫው ማሸነፍ ማግስት በከፍተኛ ደስታ ውስጥ ይገኛሉ:: አሁን ምርጫው ከተጠናቀቀ በሗላ ደግሞ ኦባማን ተስፋ በማድረግ ላይ ይገኛሉ:: እንደሚታወቀው አፍሪካችን የመልካም አስተዳደር እጦት; ረሀብ; ጦርነት [ዲሞክራቲክ ኮንጎ በዚህ ወቅት በጦርነት ላይ ናት]; የኢኮኖሚ ቀውስ; ስደት; አለመደማመጥ; በሽታ; እና ሌሎችም ነገሮች እያሰቃዩዋት ይገኛሉ::
በተለይ የሀገሬ ሰው እንደሚተርተው 'በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ'' እንዲሉ በአሜሪካ ባንኮች ላይ የደረሰውን ኪሳራ ተከትሎ በዓለም ላይ የደረሰው የኢኮኖሚ መናጋት ለአፍሪካ ትልቅ ራስ ምታት ነው:: በዚህ ወቅት አፍሮ- አሜሪካዊው የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ መጥቷል:: አፍሪካ እጆቿን ወደ ባራክ ኦባማ ትዘረጋለች... ቀጣዩን የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ዘገባ ይከታተሉ::

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ምናልባት መጠኑን በትክክል ለመናገር ያዳግት እንደሆን እንጂ በአፍሪቃ ልማት ላይም ተጽዕኖ እንደሚኖረው የሚታመን ነው። ታዲያ ይህ ስጋት አፍሪቃ ችግሩን ለመወጣት የራሷን አቅም እንድታዳብር ግፊት መፍጠሩ አልቀረም።
በአሜሪካ የቤት ባለቤቶች ዕዳና የባንኮች ክስረት ሳቢያ ዓለምን ያዳረሰው የፊናንስ ቀውስ ለአፍሪቃ ልማትም ቢቀር በአማካይና በረጅም ጊዜ ብዙ ችግር እንዳይፈጥር አሳሳቢ ነው የሆነው። ሁኔታው በተለይም የክፍለ-ዓለሚቱን የኤኮኖሚ ባለሥልጣናት ብርቱ ስጋት ላይ ሲጥል ያለፉት ዓመታት የዕድገት ሂደት እንዳይሰናከል ገቺ ዕርምጃዎችን የመውሰዱም አስፈላጊነት ጎልቶ መታየቱ አልቀረም። በዚሁ የተነሣም የአፍሪቃ የፊናንስ ሚኒስትሮችና የማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪዎች ቱኒስ ላይ ተሰብስበው መፍትሄ ለማፈላለግ ያቅዳሉ። የአፍሪቃ ሕብረት የኤኮኖሚ ጉዳይ ኮሜሣር ዶር/ማክስዌል እምኩዌዛላምባ ባለፈው ሣምንት ማብቂያ ላይ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ላይ ስላለው አመለካከት፣ በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም ሚና፣ በልማት ዕርዳታና በክፍለ-ዓለሚቱ የራስ መፍትሄ ፍለጋ ሃሣብ አዲስ አበባ ላይ ሰፋ ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር። የሕብረቱን ጥረት ዓላማም ለማብራራት ሞክረዋል።
“ስብሰባው የታቀደው በአንደኛ ደረጃ ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በአፍሪቃ ኤኮኖሚ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ መመርመር ሲሆን በአፍሪቃ የልማት ባንክ ተግባራት ላይ የሚያስከትለውን ግፊትም ያጤናል። ዓለምአቀፉ የዕርዳታ አቅርቦት ሁኔታም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው”
የአፍሪቃ ሃገራት ኤኮኖሚ ብዙም ከዓለምአቀፉ የፊናንስ ገበዮች ጋር የተሳሰረ ባለመሆኑ በዚሁ የሚገጥመው ተጽዕኖ ከባድ አይሆንም የሚሉ አይታጡም። ይሁንና በበለጸጉት ሃገራት በፊናንሱ ችግር የተቀሰቀሰው የኤኮኖሚ ቀውስ አደጋ ቢቀር በንግድና በመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የአፍሪቃው ኮሚሢዮን ባለሥልጣን ዕምነት ነው።
“ሁላችንም እንደምናውቀው በርካቶቹ የአፍሪቃ ሃገራት ከበለጸጉት መንግሥታት ጋር ብዙ የሚነግዱ ናቸው። እና በዚያ እያሰጋ ባለው የኤኮኖሚ ቀውስ የተነሣ የንግዳችን ሂደት ችግር ሊያጋጥመው ይችላል። የንግዱና የመዋዕለ-ነዋዩ ፍሰት ጉድለት በምርት ዕድገትና በሥራ መስኮች ላይ የሚከሰት ነገር ነው። እና ለብዙ የአፍሪቃ ሃገራት ሁኔታው እክል ሳይፈጥር የሚቀር አይመስለኝም”
አፍሪቃ በበለጸገው ዓለም የልማት ዕርዳታ ላይ በሰፊው ጥገኛ መሆኗ ይታወቃል። በፊናንሱ ቀውስ ሳቢያ የልማት ዕርዳታው መቀነስ ደግሞ አፍሪቃ ከ 2015 የሚሌኒየም ግቦች ለመድረስ የያዘችውን ጥረት ከንቱ ሊያደርግ የሚችል ነው። በአውሮፓና በአሜሪካ የተፈጠረው የፊናንስ ችግር በመጪዎቹ ዓመታት የመዋዕለ-ነዋይ ፍሰትንና የልማት ዕርዳታን ጋብ እንደሚያደርግ ብዙም አያጠራጥርም። የበለጸጉት መንግሥታት የልማት ዕርዳታቸውን ከፍ ለማድረግ የገቡት ቃልም ገቢር ይሆናል ብሎ መጠበቁ የሚያድግት ነው። በመሆኑም የአፍሪቃ ሕብረት የኤኮኖሚ ጉዳይ ኮሜሣር ዶር/ማክስዌል እምኩዌዛላምባ የራስን ዘዴ መመርመር ግድ ነው ባይ ናቸው።
“ችግሩን ጠለቅ አድርጎ መረዳቱ አስፈላጊ መሆኑን እንረዳለን። በመሆኑም በወቅቱ ከአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሢዮንና ከአፍሪቃ የልማት ባንክ ጋር በጉዳዩ ጥናት እያካሄድን ነው። የዚህ ጥናት ውጤት ለቱኒስ ሰብሰባ ቀርቦ ንግግር ይደረግበታል። ከዚሁ ተያይዞ የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቁዋም የ IMF ሚናም የሚጤን ጉዳይ ነው”
የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቁዋም የፊናንስ ዕርዳታ በምሥራቅ አውሮፓ በሰፊው ማተኮር በአፍሪቃውያኑ ዘንድ ችላ የመባልን ስሜት ማሳደሩ አልቀረም።
“የምንዛሪው ተቁዋም የኤኮኖሚ ዕድገትን ለማራመድ ተብሎ የሚቀርብለትን ገንዘብ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሃገራትን ለመደገፍ እንዴት በሥራ ላይ እንደሚያውል መጤን አለበት።
IMF በቅርቡ ለኡክራኒያ 16 ቢሊዮን፤ ለሁንጋሪያም 15 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ወስኗል።, በግልጽ ለመናገር ለሌሎች አገሮች በተለይም ለአፍሪቃ ብዙ ገንዘብ አይተርፍም ማለት ነው”
ምርጫው በአንድ በኩል በዓለምአቀፍ ደረጃ ተደማጭነውን ማግኘት መቻል ሲሆን ይበልጡን ግን አቅምን አሰባስቦ ችግሩን በራስ ለመወጣት ተገቢውን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ከዚሁ እንዱም የአፍሪቃን ማዕከላዊና የመዋዕለ-ነዋይ ባንኮች፤ እንዲሁም የምንዛሪ ተቁዋም በክፍለ-ዓለም ደረጃ ለመፍጠር የተያዘው ጥረት ሲሆን ይህም በመካሄድ ላይ ይገኛል። ለአፍሪቃ ልማት የሚያስፈልገውን የራስ ብቃት ለማረጋገጥ ተግባሩ መፋጠን የሚኖርበት ነው። እንደ ሕብረቱ የኤኮኖሚ ኮሜሣር ከሆነ ይህ ዕርምጃ በአፍሪቃ አገሮች መካከል ያለውን ንግድም የሚያጠናክር ሲሆን ከወቅቱ መሰል ቀውስ ምታትም ሊሰውር የሚችል ነው።
የአፍሪቃ ሕብረት ለክፍለ-ዓለሚቱ ልማት ማራመድ ከሚኖርበት ነገሮች አንዱ ውስጣዊውን ንግድ ማጠናከሩ ይሆናል። በዚሁ ረገድ የአፍሪቃ የአካባቢ የኤኮኖሚ ማሕበረሰቦች በጋራ ነጻ የገበያ ክልል ለመፍጠር በቅርቡ ካምፓላ ላይ ተስማምተዋል። የታሰበው ከሆነ በ 624 ሚሊያርድ ዶላር የሚገመት አጠቃላይ ምርት ያለውን ገበያ ትስስር የሚያሰፍን ነው የሚሆነው። የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ እንዳሉት ታላቁ የአፍሪቃ ጠላትና ዋነኛው የድክመቷ መንስዔ፤ አንድነት ማጣት፤ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ትስስር በጥቂቱ እንኳ ማስፈን አለመቻል ናቸው። ታላቅ ገበዮች ሕዝቡን ከድሀነት ለማሳቀቅ ስልታዊ መሣሪያዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።።
ነጻውን የጋራ የንግድ ክልል የሚፈጥሩት ወገኖች የምሥራቅና ደቡብ አፍሪቃ ማሕበረሰብ ኮሜሣ፣ የምሥራቃዊው አፍሪቃ ማሕበረሰብ EAC እንዲሁም የደቡባዊው አፍሪቃ የልማት ማሕበር SADC ናቸው። ትስስሩ ደረጃ በደረጃ እንዲሰፍን የታሰበ ሲሆን ትክክለኛው የጊዜ ገደብ በአንድ ዓመት ውስጥ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል። 26 ሃገራትን የሚያቅፈው ነጻ የንግድ ክልል ዕውን ቢሆን ለዕድገት ታላቅ ሚና እንደሚኖረው አንድና ሁለት የለውም። በአጠቃላይ ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በተነሳባት በአሜሪካ በባራክ ኦባማ ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ አዲስ የተሥፋ ዘመን ተከፍቷል። ተሥፋው የአሜሪካውያን ብቻ ሣይሆን የመላው ዓለም ነው። የአፍሪቃም ጭምር! ð

በኤደን ባህር በርካታ የውሃ እራት ሆኑ

በትንሾቹ የአሳ ማስገሪያ ጀልባዎች የኤደንን ባሕረ ሰላጤ ተሻግረው ወደ የመን ለመግባት ሲሞከሩ ሰጥመው ህይወታቸውን ያጡ ስድሳ የጀልባ ስደተኞች አስከሬኖች በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በየመን ጠረፍ አቅራቢያ መገኘቱን ድንበር የማይገድበው የሀኪሞች ድርጅት MSF አስታወቀ።
ከሱማሊያ ወደ የመን ለመግባት ሲሞክሩ በባህር ሰጥመው ሲሞቱ እነዚህ የመጀመሪያዎቹ አለመሆናቸውን የጠቆመው MSF በዚህ ዓመት ብቻ ከ400 በላይ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ስደተኞች በዚህ ባህር ውስጥ ሰጥመው ቀርተዋል:: አሁን ከሞቱት ወደ ስድሳ የሚጠጉት ስደተኞች መካከል ምን ያህሉ የሶማሌያ: ምን ያህሉ የኢትዮጵያ ስደተኞች መሆናቸው አልታወቀም:: በየመን የሚገኙት የድርጅቱ ባለስልጣን አንድሪያስ ኩፒፓስ ለጀርመን የዜና ወኪል እንዳስረዱት፡ ስደተኞቹ የሞቱት ህገ ወጦቹ የጀልባዎቹ ሰራተኞች በተለያየ ምክንያት ባሕር ውስጥ እንዲዘሉ ባስስገደዱበት ጊዜ ነበር።
በሕገወጥ መንግድ ባህርን አቋርጦ የአንድን ሀገር ድንበር ሰብሮ ለመግባት በሚደረግ ትግል ምናልባት ድንበር ጠባቂ ፖሊስ እጅ ላለመግባት ሲሉ የጀልባዎቹ ሰራተኞች (ደላሎች) ስደተኞችን ወደ ባህር እንዲሰምጡ እንደሚያስገድዷቸው ያወሱት እኚሁ ባለስልጣን በተለይ በዚህ አመት በኤደን ባህር የሞቱት ቁጥር ከፍ ማለቱ አሳስቧቸዋል:: በሀገር ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቋቋም የተሳናቸው ኢትዮጵያው ያን: ኤርትራዊያን: ሶማሊያውያን ስደተኞች በሊቢያ ወደ ጣሊያን: በሞሮኮ ወደ ስፔን: በቱርክ ወደ ግሪክ ለመግባት በሚያደርጉት የባህር ጉዞ በርካቶች ለሞት ይዳረጋሉ::
እነዚህ ሁሉ መከራዎች አልፈው ለስኬት የበቁ ጥቂት ሰዎች እንደሚናገሩት ""የአንድን ሀገር ድንበር ስታቋርጥ መሞት: መታሰር ወይም የምትፈልገው ሀገር መድረስ ይኖራል:: እነዚህን ሁሉ ለማድረግ ገንዝብ ያስፈልጋል:: የምታቋርጠበት ሀገር ፖሊስ ገንዝብ ከፍለህ እዛ እንደደረስክ ስለሚያውቅ ሊረዳህ አይችልም:: እንደውም ገንዝብ ካልከፈልክ እስር ቤት ትማቅቃለህ"" ይላሉ::
በየመን የኤደን ባህረ ሰላጤን አቋርጠው ምናልባት ከሞት እና በፖሊስ ካለመያዝ ቢተርፉ እንኳ የመን ውስጥ ገብቶ ሥራ ሰርቶ ለመኖር እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ በርከት ያሉ በስፍራው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ይናገራሉ:: በዩናይትድ ኔሽን ተመዝግቦ እንኳ ወደ 3ኛ ሀገር ለመሄድ በየመን እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳለ የሚናገሩት ስደተኞች ''የየመን ፖሊሶች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰጠውን የስደተኛነት ወረቀት እስከመቅደድ ይደርሳሉ:: ለዚህም የሚናገራቸው የለም"" ይላሉ:: አንድ በሱማሊያ አድርጎ የመን የገባ ስድተኛ ሲናገር ''ሞትን አምልጬ የመን ገባሁ: አሁንም ላለመሞት እየታገልኩ ነው"" ይላል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ሕትመት እየገባን ባለንበት ወቅት የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ባሰራጨው ዘገባ በዚሁ በየመን የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ላለመያዝ ፣ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ሰዎችን በአደን ባህረ-ሰላጤ በኩል ወደ የመን የሚያሸጋግሩ ሰዎች 240 ስደተኞች ከመርከብ ወደ ባህር አየዘለሉ እንዲዋኙ በማስገደዳ ቸው 18 ሲሰጥሙ ከ 70 በላይ የሚሆኑት ደብዛቸው መጥፋቱ ተነገረ። የተረፉት ደቡብ የመን ከተማ ፣ አህዋር መግባታቸው ተገልጿል። ስደተኞቹ፣ በአመዛኙ ከሶማልያ ጥቂቶቹም ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ ተመልክቷል። ð

የውጭ ምንዛሬ እጥረት በኢትዮጵያ ተከሰተ

በኢትዮጵያ የተከሰተዉ የዉጪ ምንዛሪ እጥረት በመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች ላይ አሉታዊ ተፅኖ እያሳደረ ነዉ:: ዛሬ የሀገሪቱ ሕዝቦች ችጋር እና የኑሮ ውድነት ስንግ ይዟቸው መንግስት በፍጠረው ችግር ምክንያት ከዓለም የደሀዎች ደሀ የምትመደበው ሀገራችን ይህ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መከሰቱ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል::
የመንግስት ባለስልጣናት ''በእኛ አመራር የመጣ ልማት ነው; ኢኮኖሚያችን ከሚገባው በላይ አድጓል"" እያሉ በሰፊው እየተናገሩ ቢሆንም ችግሮች አግጥጠው እየታዩ ይገኛሉ:: ረሀብ እና የኑሮ ውድነት እያሰቃየው ያለው ሕዝብ ችግሬ ከዛሬ ነገ ይቃለላል እያለ በተስፋ እየተጠባበቀ ባለበት ወቅት የውጭ ምንዛሬ በሀገሪቱ ባለመኖሩ ፋብሪካዎች በአደጋ ላይ ሲሆኑ ሰራተኞችም በመበተን አደጋ ውስጥ ወድቀዋል::
ሙሉ ለሙሉ በብሔራዊ ባንክና በንግድ ባንክ ውስጥ የውጭ ምንዛሬ የሌለ በመሆኑ ነጋዴዎች ጥሬ እቃ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ከመቸገራቸውም በላይ በሀገር ውስጥ የተሰማሩበት ሥራ በመቆሙ ሀገሪቱ ወትሮ ከነበረችበት ችግር የባስ አዘቅት ውስጥ እየገባች መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ::
ነዳጅ በዓለም አቀፍ ላይ ከ50 ዶላር በታች እያሽቆለቆለ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ግን በሚገርም ሁኔታ ላይ ነው ያለው:: በአሜሪካ ከሁለት ወር በፊት ከነበረው የነዳጅ ዋጋ አሁን በግማሽ ያህል እየተሸጠ ሲሆን በኢትዮጵያ ግን በሳንቲም ደረጃ ቅናሽ ያደረገው:: ይህ የሆነበት ምክንያት የረከሰውን ነዳጅ ለመግዛት የውጭ ምንዛሬ ስለሌላቸው በነዳጅ እጥረት ሕዝቡ እየታመሰ ይገኛል::
አሁን የተከሰተው የውጭ ምንዛሬ እጥረት መንግሥት የልማት እቅዶቹን በቁነና እንዲያፅ ፈፅም ወይም በጣም-አስፈላጊና አስፈላጊ የሚል ቅደም ተከተል እንዲያወጣ እያስገደደዉ ነዉ:: ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖችና የምጣኔ ሐብት አዋቂዎች እንደሚሉት በእጥረቱ ምክንያት መንግሥት በጣም አስፈላጊ ለሚላቸዉ የልማት ፕሮጄክቶች ቅድሚያ እንዲሰጥ አስገድዶታል:: ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ደሀ ሕዝብ በእጅጉ ይጎዳል:: መንግስት የምንዛሬው እጥረት የመጣበትን ምክንያት በውል እንደማያውቅ ቢገልጽም ተቃዋሚዎች ግን ''በብድር እና በእርዳታ የሚመጣውን የውጭ ሀገር ገንዝብ በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም እየቦጠቦጡ በውጭ ሀገር ባንኮች ውስጥ እያከማቹ ሀገሪቱን ባዶ በማስቀረታቸው የንግዱ ማሕበረሰብ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳያድግ ሲገደብ; አሁን ደግሞ ብዙ ፋብሪካዎች ለመዘጋት እንደተገደዱ'' ይናገራሉ::ð

ኦባማ በድሬደዋ


ከሮቤል ሔኖክ
ድሬደዋ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ በአስተዳደር የምትመራ ሁለተኛዋ ከተማ ናት:: ድሬደዋ ከኦሮሚኛ ወደ አማርና ሲተረጎም "የመድሀኒት ሜዳ" ማለት ሲሆን ከሶማሊኛ ወደ እንግሊዘኛ ሲረጎም ደግሞ "the place that Dir conquered or hit with his spear" የሚል ትርጓሜ እንዳለው በሱማሊኛ የተጻፉ ጽሁፎች ይጠቁማሉ::
የድሬደዋ አስተዳደር በሁለት ወረዳዎች የተከ ፈለ ሲሆን አንደኛው ኢሳ ሁለተኛው ጉርጉራ ይሰኛሉ:: በኢትዮጵያ ፓርላማ 2 መቀመጫ ቦታም አላቸው:: በድሬደዋ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ሲገኝ በከተማዋ ደግሞ 'አባ ጤና ደጃዝማች ይልማ ኢንተርናሽ ናል ኤርፖርት""; አንድ ስታዲየም; የምድር ባቡር እና የተለያዩ የገበያ ቦታዎች ይገኛሉ::
የአዲስ አባባ ጅቡቲ ምድር ባቡር መስመርን ተከትሎ በ1902 አ.ም የተቆረቆረችው ድሬደዋ ከአስር አመታት ወዲህ ለሁለት ጊዜያት በጎርፍ አደጋ መመታቷ የሚዘነጋ አይደለም:: በነዚህ የጎርፍ አደጋዎች በርከት ያለ ሰው ሕይወት እና የንብረት ላይ አደጋ ከመድረሱ በተጨማሪ ለብዙዎች መሰደድ ምክንያት ሆኗል::
በወቅቱ የዓለማችንን ሚዲያ ትኩረት ሥቦ የነበረው የድሬደዋ በጎርፍ አደጋ መጥለቅለቅን ተከትሎ ዛሬ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ባራክ ኦባማ በሥፍራው ተገኝተው መመልከታቸውን የምናስታውስ አለን? በፎቶ ግራፉ ላይ የምንመለከተው ኦባማ ኦገስት 30 2006 በድሬ ደዋ ከተማ በጎርፍ አደጋ የደረሰባቸውን አካባቢዎች ሲጎበኙና አደጋ የደረሰባቸውን ወግኖቻችንንም ሲያጽናኑ ነው:: በፎቶ ግራፉ ላይ አብረዋቸው የምናያቸው ኢትዮጵያውይው አቶ አበራ ቶላ ሲሆኑ እኚህ ሰው የኦክስፋም አሜሪካ የቀጠና ዳይሬክተር ናቸው:: አቶ አበራ ቶላ ለኦባማ ስለደረሰው አደጋ ገለጻ አድርገው ኦባማን አስጎብኝተዋል:: ኦባማም ኦክስፋም አሜሪካ በድሬደዋ በወቅቱ በደረሰው አደጋ ላደረገው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አድርሰዋል:: ዛሬስ?
150 ሰው ያለቀበት: ከ12ሺህ ሰዎች በላይ ጉዳት ባደረሰው አደጋ ወቅት ኦባማ እንደደረሱት በኢትዮጵያ መልካም አስተዳድር ሰፍኖ አንጨላጭሎ የነበረው የዴሞክራሲ በር እንዳይዘጋ ምን ያግዙን ይሆን? በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ ብዙዎች የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከምርጫው በፊት ኢሕአዴግ ለዴሞክራሲ የከፈተው በር አሁን ጥርቅም ተደርጎ ተዘግቷል:: ኦባማ ልክ በድሬደዋው አደጋ እንደደረሱት ሁሉ ዛሬም በኢትዮጵያ ለሰብአዊ መብቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብለን እንጠብቅ??
በነገራችን ላይ ድሬደዋ ከአዲስ አበባ 310 ማይልስ ርቀት ላይ የምትገኝ ከታላላቅ የኢትዮጵያ የንግድ ከተሞች መካከል አንዷ ናት:: በድሬደዋ አስተዳደር ካውንስል ውስጥ ካሉት ሕዝቦች መካከል 40% ኦሮሞዎች: 27.7% አማሮች: 13.9% ሶማሊዎች: 4.5% ጉራጌዎች (2.3% ሰባት ቤት: 0.8% ሶዶ: 1.4% ስልጤ) እና 5.9% የሌሎች ብሄሮች ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ:: የድሬደዋ ዋና ብሔራዊ ቋንቋ አማርኛ ሲሆን 63.2% የእስልምና; 34.5% የኦርቶዶክስ ክርስቲያን; 1.5% የፕሮቴስታንት; 0.7% የካቶሊክ እና 0.1% የሌሎች እምነት ተከታዮች ይኖራሉ::ð

ቴዲ አፍሮ በአንካሳው ሕግ ጥፋተኛ ተባለ


"አብረን ከሮጥን እርሱን አስቀድመዋለው"" ሲል ጀግናው የኢትዮጵያ አትሌት ሀይሌ ገብረ ሥላሴ ያወደሰው በዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ከፍተኛ የክብር ቦታ የሚሰጠው ተወዳጁ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ""እውነትን በዜማ የሚናገር የሕዝብ ልጅ"" ሲሉ ብዙሀኖች ያወድሱታል:: ድምጻዊ: የዜናማና የግጥም ደራሲ በመሆን ተፈጥሮ ሁሉን አሟልታ የሰጠችው የሚባልለት ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ “ሰው ገድለሀል ተብሎ በተጠረጠበት “ወንጀል” ቴዲ አፍሮ ጥፋተኛ ተባለ። ፍርዱ ዲሰምበር 5 የሚሰጥ ሲሆን እና የዲሴምበር አንዱን ችሎት በገጽ 3 ላይ ይከታተሉ። ""የመለስ አስተዳደር ድራማ ሲሰራ አሰራሩን አያውቅበትም"" ነበር ያለችው ችሎቱን የተከታተለች አንዲት ወጣት:: ""ድራማቸው ሁሉ የሕጻናት ስለሆነ ሁልጊዜ ይጋለጣሉ"" የምትለው ይህችው ወጣት ከዲሴምበር አንዱ የቴዲ ችሎት በፊት በሕዝቡ ላይ እየተደረገ የነበረው ነገር ሁሉ በቴዲ ላይ ቀድሞ የተጻፈ ነገር እንደሚፈረድበት ያስታወቀ ነበር ትላለች::ከጥቂት ቀናት በፊት መሰብሰብ የተከላከለው ሕዝባችን በመስቀል አደባባይ ለታላቁ ሩጫ በተሰበሰበት ወቅት ''ቴዲ ኦባማ; መለስ አሳማ"" እያለ እየዘፈነ ብሶቱን ሲያሰማ የቴዲን ቲሸርት የለበሰ; ስለቴዲ ጮክ ብሎ የተናገረ አይን እና ጆሮ በሌላቸው የፌደራል ፖሊሶች ተወግረው እስር ቤት አድረው; ፈርመው መለቀቃቸው በአንድ ''ሰውን ገጭተሀል ለተባለ እስረኛ'' የማይገባ ነገር ነበር:: ድራማው ይህ ነው የምትለው ወጣት ከጥቂት ቀናት በፊት በኢንጂነር ሀይሉ ሻውል የሚመራው የመኢአድ ፓርቲ በአደባባይ በአይሱዙ መኪና የቴዲ አፍሮን 'ጃ ያስተሰርያል" ሙዚቃ ከፍቶ ስለ ሰላማዊ ትግል በመቀስቀሱ ዘፈኑን ከፍተው መቀስቀስ እንደማይችሉ ፖሊሶች ገልጸው ቅሰቀሳውን ያፈኑ ሲሆን ከቀናት በሗላ ያቺው ለቅስቀሳ የወጣችው አይሱዙ መኪና የቴዲ ዘፈኖች ስለተከፈተና ስለተቀሰቀሰባት ብቻ መኪናው ታስሯል:: እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች እንዲሁም ቴዲ ችሎት በቀረበ ቁጥር ችሎቱን የሚከታተል ሰው ካለፈቃዱ ቪዲዮ መቀረጹ አሁንም በትራፊክ ሕግ መጣስ ለተከሰሰ የማይገባ ነው ትላለች ይህችው ወጣት:: እነዚህ እና ሌሎችምክንያቶች ተደማምረው በቴዲ ላይ የቀረበው ክስ ሙሉ በሙሉ ፖለቲካዊ ይዘት እንዳላቸው ትናገራለች::ዲሴምበር 1 በዋለው ችሎት ላይ የሕወሐት አባሉ ዳኛ አቶ ልኡል ገብረማርያም ካለምንም ማገናዘብ ግልጽ የሆኑ ማስረጃዎችን በቅንነት ባለመተርጎም በአርቲስቱ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ወስነዋል:: እኚህ ዳኛ በቴዲ ላይ ለመፍረድ ከተቀየሩበት ችሎት መምጣታቸው ሌላው ድራማ ሲሆን ዳኛው ከዚህ ቀደም በመንግስት ላይ ጥቂት ተቃውሞ ባላቸው ሰዎች ላይ በአንካሳው ሕግ በመፍረድ ይታወቃሉ:: በውስጥ ገጾች ላይ ይመልከቱ:: አርብ ዲሴምበር 5 ፍርድ የሚጠብቀው ቴዲ በፍርድ ቤቱ የጥፋት ማቅለያ አቅርብ ቢባልም ""በሐቅ ለማይፈርድ ፍርድ ቤት ምንም አይነት የቅጣት ማቀለያ ከዚህ በላይ የለኝም:: እውነት ምንጊዜም ታፍና አትቀርም እኔ ንጹህሰው ነኝ'፤ ማንንም ሰው አልገደልኩም'; ብሏል:: በፖሊስ ታጅቦ እየሄደ ባለበት ወቅትም ለተሰበሰበው ሕዝብ ‘ከ እንግዲህ ያላችሁኝ እናንተ እና ፈጣሪ ብቻ ናችሁ” ሲል መናገሩን ሪፖርተራችን ከአ.አ ዘግቧል።ቴዲ አፍሮ ላይ ለመፍረድ በአንካሳው ሕግ የተቀመጡት አቶ ልኡል ጥፋት ማቀለያ ቀረበም አልቀረበም አርብ እለት የተጻፈላቸውን ፍርድ ለቴዲ ማንበባቸው አይቀሬ ነው:: ብዙዎች ቴዲ ""17 መርፌ ብሎ ዘፍኖ 17 ዐመት ሊፈርዱበት ነው"" እያሉ እንደቀልድ ቢጤ ጣል ቢያደርጉም ልጁ በተጠቀሰበት አንቀጽ ከ5 እስከ 15 ዐመት ይፈርዱበታል ተብሎ ይጠበቃል:: የዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ያነጋገራቸው የፖለቲካ ምሁራን እንደሚሉት በቴዲ ላይ እየደረሰው ያለው ነገር ነገ ማንም ዘፋኝ ተነስቶ ሰለፖለቲካ እንዳይዘፍን እና መንግስትን በዘፈን እንዳይቃወም ታቅዶ የተደረገ ነው:: ሆኖም ግን ይላሉ እነዚሁ ምሁራን ''ሆኖም ግን በልጁ ላይ የተፈረደው ፍርድ ሕዝቡን የበለጠ በስርአቱ ላይ እንዲነሳና የትግሉን መንፈስ ያጠናክራል"" ይላሉ:: በሌላ በኩል ቴዲ አፍሮ ወንጀሉን ሰርቷል ብለው የሚያምኑ ወገኖች ''የፈሰሰው የደሀ ነፍስ እስከሆነ ድረስ ቴዲም እንደማንኛውም ሰው ፍርዱን መቀበል አለበት::'' ይላሉ::ምስክሮች ሟች ደጉ ይበልጣል አስከሬኑ ለምርመራ ምኒልክ ሆስፒታል በጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. ገብቶ፣ በጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ምርመራ እንደተደረገለት የሚገልጸውን ማስረጃ ቢሰጡም; (አርቲስቱ ከውጭ ሀገር የገባው ጥቅምት 23 ነው) ፖሊስ ሰነዱን በሀይል ደጉ ይበልጣል የሞተው ጥቅምት 23 እንደሆነና የሬሳ ምርመራ የተደረገለትም በ24 እንደሆነ አስደርጎ ሰነዱን ማስቀየሩ በግልጽ በፍርድ ቤት ቢመሰከርም; ዳኛው ልኡል ነውና ጥፋተኛ ነህ ብሎታል:: ቴዲ አፍሮ አርብ የሚፈርድበትን ፍርድ ለማወቅ ወደ ዘ-ሀበሻ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከአርብ ከሰአት ጀምሮ ብትደውሉ መረጃ እንሰጣችሗለን::በሌላ በዘገባው አቃቤ ሕጉ ማነው? ዳኛው ልዑል ገ/ማርያምስ ማነው? ከዳኛው የሚጠበቅ ፍርድ ተሰጠ ወይ? የሚሉ ምርጥ እና ወቅታዊ ሁሉን አቀፍ ሚዛናዊ ዘገባ ይዘናል ይከታተሉን::የቴዲ አፍሮ ክስ አቃቤ ሕግ ማነው?በሻሸመኔ ከተማ ተወልዶ የመጀመሪያ ትምህርቱን እዛው አጠናቆ ከ7ኛ እና 8ኛ ክፍል በሗላወደ አሩሲ ያመራው ይህ ሰው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአሰላ ከተማ ተከታትሏል:: ከዛም በ1992 ከአዲስ አበባዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት የተመረቀው የቴዲ አፍሮን ክስ በአቃቢ ሕግነት የሚመራው ፈቃዱ ጸጋ ነው:: አቃቤ ህጉ የቴዲ አፍሮንክስ ማን ነው የሠራው?? በሚል በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ልዩ ዘጋቢ ለቀረበለት ጥያቄ ''ክሱን እኔ አላዘጋጀሁትም::ክስ በፖሊስ ተዘጋጅቶ ለአቃቤ ሕግ ይቀርባል:: አቃቤ ህግ ያስከስሳል አያስከስስም የሚለውን መርምሮ ለፍርድ ቤትያቀርባል::'' ብሏል::ቴዲ አፍሮ በተከሰሰበት ወንጀል ዓይነትከዚህ በፊት ታዋቂው አትሌት ተስፋዬቶላ በዋስ ተለቆ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ ሲከታተል ነበር; አሁን ለምን ቴዲ አፍሮ ለምን ታስሮ እንዲከታተልሆነ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቃቤ ህጉ ''በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ተስፋዬ ቶላ መንጃ ፈቃድ ነበረው'' በሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል:: ተባባሪ ዘጋቢያችን ለአቃቤ ህጉ ከዚህ በፊት በዚሁ ክስ ቴዲ አፍሮ በ15 ሺህ ብር ዋስ መለቀቁን አስታውሶ ለምን ያን ጊዜ ተለቆ አሁን ይታሰራል? የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር:: አቃቤ ህግ ፈቃደ ጸጋ ''አዎ ከዚህ በፊት በዋስትና ተለቆ ነበር:: ከአሁኑ ጋር ልዩነት አለው:: ያኔ ገና የፖሊስ ምርመራ ላይ ነበር:: ምርመራው ካላለቀና ጉዳዩ ተጠርጣሪውን ያስከስሰዋል ወይስ አያስከስሰውም የሚለው ጥያቄ ገና ካልተወሰነ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጥሮ ይሰጣል:: በዚያ ጊዜ ተጠርጣሪው በዋስትና ይለቀቃል ወይም አይለቀቅም የቴዲ ቁርጥቀን... ከገጽ 1 የዞረተብሎም በፍርድ ቤት ይወሰናል:: ጉዳዩ በፖሊስ ነው የሚከናወነው:: በዋስትና ተለቀቀ ማለት ጉዳዩ የሚያስከስስ ሆኖ ከተገኘ ወደ ተከሰሰበት ቦታ እንዲቀርብ ዋስ ጠራ ማለት ነው:: ከዚያ በሗላ ምርመራው አልቆ ወደ አቃቤ ሕግ ይመጣል:: ፖሊሶች በምን እንደሚከሰስ ስለማያውቁት ነው ዋስትና አስጠርተው የሚለቁት:: አቃቤ ህግ ነው ሁሉን መርምሮ ከህግ ጋር አያይዞ የሚከሰው:: በተጠቀሰው አንቀጽም አቃቤ ሕግ ዋስትና እንዲከለከል ይጠይቃል'' ብለዋል::አዲስ የወጣው የኢትዮጵያ የትራፊክ ሕግ ከሁለት ሰው በላይ ገጭቶ በመግደል የተጠረጠረ ወይም በመጠጥ ሀይል ሲያሽከረክር ሰው የገደለ ሰው የዋስትና መብቱ ይከለከላል ይላል:: ቴዲ የተጠረጠረው በአንድ ሰው መግደል ነውና ለምን በዋስ እንዲከታተል አልተደረገም ለሚለው ጥያቄ ''ዋስትና የሚያስከለክለውም የሚፈቅደውም ሕጉ ነው:: እኛ ቴዎድሮስ ካሳሁን ላይ የጠቀስነው የወንጀል ሕግ 543 ንኡስ ቁጥር 3 ነው:: አራት ነገሮች ተጠቅሰዋል:: ከአንድ በላይ ከገደለ ወይም ግልጽ የሆነ ደንብ ተላለፎ ወንጀሉን ከፈጸመ ወይም የሚያሰክር ነገር ወሶድ ወንጀሉን ከፈጸመ ወይም የሚያፈዙ እጾችን ወስዶ ወንጀሉን ከፈጸመ የሚሉ ናቸው - 4ቱነጥቦች:: ከእነዚህ መካከል አንዱን የሚያሟላ ከሆነ ዋስትና ያስከለክላል:: በቴዎድሮስ ላይ የጠቀስነው ወንጀል ግልጽ የሆነ ደንብ ተላልፏል ብለን ነው:: መኪና ለማሽከርከር ከሚመለከተው ባለስልጣን መ/ቤት መንጃ ፈቃድ ሊሰጠው ይገባል:: ግን መንጃፈቃድ አልተሰጠውም ተብለናል:: ስለዚህ ያለመንጃ ፈቃድ ነው የትራፊክን ደንብ በማፍረስ የተከሰሰው:: ይህ ወንጀል ከ5 እስከ 10 ዓመት ያስፈርዳል:: የሰው ሕይወት ያለፈበት ደግሞ እስከ 15 ዓመት ያስቀጣል:: ስለዚህ ዋስትና ያከለከለው ዳኛው; አቃቤ ህጉ አይደሉም:: ህጉ ነው'' ሲሉ አብራርተዋል::ከፍርዱ ቀን አስቀድሞ የቴዲ አፍሮ ፍርድ ደርሷል:: ለመጨረሻ ቀጠሮ ተቀጥሯል ከፍርዱ ምን ይጠብቃሉ የሚል ጥያቄ ለአቃቤ ህጉ ቀርቦላቸዋል:: ''አድናቂዎቹም ሆኖ ሌሎች ሰዎች ማየት ያለባቸው ነገር አለ:: ቴዎድሮስ ታዋቂ ነው; ግን ታዋቂ ሰው ወንጀል አይሰራም የሚል ነገር የለም:: ይሄንን ወንጀል ሆነ ብሎ ፈጽሞታል የተባለ አይደለም; በቸልተኝነት ፈጽሞታል ነው የተባለው:: ቸልተኝነት ደግሞ ከሰው ባህሪይ የሚመጣ ነገር ነው:: ነገር ግን ቸልተኛ ላለመሆን መሞከር ነበረበት ነው; የክሱ ሀሳብ:: በእርግጥ በሁሉም ነገር ቸልተኛ ስለሆነ አይቀጣም ግን በቸልተኝነት ያደረሰው ጉዳት ይታያል:: ዋናው ነገር ቴዎድሮስ ታዋቂ ስለሆነወንጀል ሊሰራ አይችልም; ከሰራም ሊጠየቅ አይገባም ማለት ተገቢ አይደለም:: እንደማንኛችንም የሰው ፍጡር ነው ብሎ ማሰብ ነው የሚገባን:: በእኛ በኩል ወንጀሉን ሰርቶ ከሆነ በደጋፊዎቹ እምነት ወንጀሉን አልሰራም ከሆነ ሁሉን ነገር ማስረጃ ነው የሚወስነው'' ሲሉ ''የዳኛው መቀየር በፍርዱ ላይ ምን ተጽእኖ ያመጣል; በተለይ ዳኛው አቶ ልኡል የፖለቲካ ሰው ነው ተብሎ ይነገራልና'' በሚለው ላይ አስተያየት ለመስጠት እንደማይፈልጉና ተገቢው ፍርድ ይሰጣል፤ ፍርዱንም ማንም መቀበል አለበት ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል::ዳኛው አቶ ልዑል ገ/ማርያምበመጨረሻው ሰአት ፍርዱን እንዲሰጡ ከሌላ ቸሎት ተቀይረው የመጡት አቶ ልዑል ከዚህ ቀደም በኦነግ ጉዳይ; በኡጋዴን ነጻ አውጪ ተከሳሾች ላይ; በቅንጅት መሪዎች ላይ; በበርካታ ጋዜጠኞች ላይ እድሜ ልክ እና የረዥም ዓመት ክስ የፈረዱ አንባገነን ዳኛ ናቸው ይሏቸዋል እርሳቸውን የሚያውቁዋቸው:: አቶ ልዑልን የሚያውቋቸው ሰዎች እንደሚናገሩት ገዢው ፓርቲ የሚፈልገውን ሕግን አጣሞ የመፍረድ ሥራ እንዲሰሩ በቦታው ላይ የተቀመጡ ናቸው:: አሁንም በመጨረሻው ሰዓት የቴዲ አፍሮ ክስ እኚሁ ዳኛ እጅ ላይ መውደቁ ትክክለኛ ፍርድ ይሰጣል ተብሎ እንደማይጠበቅ ብዙሀን ይመሰክራሉ:: ከዚህ ቀደም በአቶ ልዑል ዳኝነት 5 ዓመት እስር ቤት ቆይቶ የወጣ አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኛ 'በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ሄሊኮፕተር ተመቶ መወድቁን መዘገቡን" ተከትሎ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርቦ ዳኛው "የሄሊኮፕተሩን ስባሪ አምጣ'' እንዳሉት ገልጾ; በዚህ የተነሳ 5 ዓመት እስር ቤት ቆይቶ ወጥቷል:: በጣም የሚገርመው ይህ ሂሊኮፕተር መወደቁ እውነት መሆኑንና በጦርነቱ ወቅት አብራሪው በዛብህ ጴጥሮስ (የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ወንድም) እስካሁን በኤርትራ መንግስት እጅ የት እንደተሰወሩ እንደማይታወቅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን ሁሉ ሲነገር ነበር:: በበርካታ ሀገር ወዳድ ወገኖች ላይ አሰቃቂ ፍርድ የሰጡት አቶ ልኡል በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሔኖክ አለማየሁ ላይም በትራቸውን አሳልፈዋል:: እኚህ ዳኛ ጋዜጠኛውን በኢትዮጵያ እያለ በሚያሳትመው መዲና ጋዜጣ የተነሳ በጋዜጣው ላይ 'የደህነንት ሚንስትሩን አቶ ክንፈ ገብረመድህንን እነማን ገደሉት?' በሚል ባወጣው ምስጢራዊ ዘገባ በዚህ ግድያ ላይም የኢትዮጵያ ገዥ ባለስልጣናት እጅ እንዳለበት በመጻፉና በማጋለጡ ለ3 ቀናት በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ በጨለማ ክፍል ከታሰረ በሗላ በ5ሺህ ብር ዋስትና መለቀቁ; በፍርድ ቤት ቆይታውም የክሱ አዝማሚያ ፖለቲካው ይዘትን እየያዘ በመምጣቱ ከሀገር በዚህ እና በሌሎች 12 ክሶችየተነሳ መውጣቱን ጋዜጠኛው ይናገራል:: በሌላ በኩልም ሔኖክ ከሕወሓት ከተገነጠሉትና እስር ቤት ተወርውረው ከነበሩት ከአቶ ስዬ አብርሃ ጋር በማእከላዊ ምርመራ ማስተባበሪያ በታሰረበት ወቅት እኚህን የቀድሞ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ከ እስር ቤት ቃለ-ምልልስ አድርጎ በጋዜጣው ላይ በማተሙ በተከሰሰበት ክስ አቶ ልኡል ሄኖክን በ5 ሺህ ብር ዋስ አስይዞ ከእስር እንዲወጣ አድርገዋል። አንድን ሰው ኢንተርቪው አድርገሃል በሚል መክሰስና ይህን በሚያህል ብር በዋስ መልቀቅ አሳፋሪም አስገራሚም ነገር ነው። ጨርሶም መክሰስ አይገባም።አቶ ልዑል የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች በሙሉ ክስ እርሱ በሚቀመጥበት ችሎት እንዲታይ ተደርጎ በየጋዜጠኛው ላይ የቂም በቀል ፍርድ ሲሰጥ የከረመ ሲሆን በዚህም በጋዜጠኞች ዘንድ አንድ ክስ እርሱ ችሎት ከደረሰ ''አለቀልህ'' ተብሎ ፍርዱን ቀድሞ ማወቅ እንደሚቻል ይነገራል:: በጋዜጣ ላይ የጋዜጣ ቀን አልጻፍክም ብሎ ካለምንም ማስጠንቀቂያ 2000 ብር የሚፈርደው አቶ ልኡል እጅ የገባ ክስ የፈለገ ማስረጃ ቢቀርብ ነጻ አይወጣም; ይልቁንም ስንት አመት ይፈረድብኝ ይሆን? ብሎ ማሰብ ይቀላል የሚሉ ብዙ ናቸው::ቴዲ አፍሮ የምስክርነቱን ቃል ሲሰጥ:- ”በጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገባሁ። ምትኩ ግርማ የተባለው ጓደኛዬ ከማናጀሬ ቀጥሎ ጉዳዬን የሚፈጽምልኝ ሲሆን፣ በዕለቱ ከኤርፖርት ከተቀበለኝ በኋላ ሚኪስ ፋሽን የተባለ ልብስ ቤት ሄደን ልብስ ገዛሁ። ምሳ ከበላን በኋላ ወደ ያሲን ቤት ሄድኩ። ከዚያም እዚያ ውለን ወደ አራት ሰዓት አካባቢ ማምሻውን ከያሲን ቤት ወጥተን መስቀል ፍላወር አካባቢ ያለ ቤት አመሸን፣ በኋላ ሳምሶን የተባለ ጓደኛዬ መጥቶ ነበር። ከለሊቱ 9 ሰዓት አካባቢ ሲሆን ከዛ ወጣን፣ እኔና ሳምሶን ኦሎምፒያ ድረስ አብረን ሄድን፣ እኔ የማሲንቆ ጨዋታ እወድ ስለነበር ወደ ካሳንችስ ይወዳል ቤት እየነዳሁሄድኩ። እዚያ ከደረስኩ በኋላ ሃሳቤን ቀየርኩና ወደ ቤቴ ሲ.ኤም.ሲ መንገድ ጀመርኩ፣ ምንግዜም ከውጭ ስመጣ የሄድኩባቸው ሀገራትና የዚህ ሀገር የእንቅልፍ ሰዓት ለማስተካከል ስለሚከብደኝ ነበር ቀኑን ውጭ ያሳለፍኩት። እንደሚታወቀውና ሐኪምም እንደሚለው እንዲህ ዓይነት የእንቅልፍ መዛባት ሲገጥም መኪና መንዳት አደጋ ሊያጋጥም ይችላል። በዚህ ላይ ውጭ በነበርኩበት ግዜ ተጀምሮ በምኖርበት ሲ.ኤም.ሲ. አካባቢ የመንገድ ኮንስትራክሽን ሥራ ተጀምሮ ስለነበር አባጣና ጎርባጣውን መንገድ አላየሁትም ነበርና ከለሊቱ 9 ሰዓት አካባበቢ ከግዑዝ ነገር ጋር ተጋጨሁ። በሰዓቱ ብዙ ነገሮችን ወደሚረዳኝ ምትኩ ጋር ደወልኩ፣ስልኩን ሊያነሳልኝ አልቻለም። መኪናዬ ውስጥ ያሉትን ካሴቶቼንና ወረቀቶቼን ሰብስቤ በላስቲክ ካደረኩ በኋላ ሠፈራችን ያለ የፔፕሲ ሠራተኛ አግኝቶኝ በመኪናው ወደ ቤቱ ወሰደኝ። ጠዋት ምትኩ የደወልኩለትን ስልክ አይቶ ደወለለኝ። የደረሰብኝን ነገርኩትና መኪናዋ መንገድ ዘግታ ስለቆመች እንዲያስጎትትልኝ ነገርኩት። በኋላ ላይ መኪናው በትራፊክ ጽሕፈት ቤት ሲያልፍ ታርጋ የለውም ተብሎ መታሠሩን ሰማሁ። ሌላ አንድ ላስገነዝብ የምፈልገው ነገር እኔ ሀገር ውስጥ የገባሁት በጥቅምት 23 ቀን ነው፣ የምኒልክ ሆስፒታል ማስረጃ እንደሚያስረዳው ደግሞ ሟች የሞተው በጥቅምት 22 ቀን ነው።” ብሏል:: አቶ ልዑል የፈለገ ማስረጃ ቢቀርብ ማስረጃውን እንደ እራሱ አመለካከት የሚመለከት እንጂ የሚያገናዝብ እንዳልሆነ በቴዲ አፍሮ ፍርድ ላይ አሳይቶአል የሚሉ ወገኖች አሉ። ዳኛው በተለምዶ እንደታየው ነገሮችን በሙሉ በቅንነት የመተርጎም ባህሪይ የለውም። ዳኛ ለተከሳሽም ለከሳሽም እኩል እንደሆነ የማይገነዘበው ከአቶ ልዑል እጅ መልካም ፍርድ መጠበቅ፤ መለስ ዜናዊ የሚተርትባቸው እነዛ ትላልቅ ግመሎች በመርፌ ቀዳዳ እንዲሾልኩ እንደመጠበቅ ይቆጠራል የሚሉ በርካታ ናቸው።ከአሁን በሁዋላ ምን ይጠበቃል? በሚለው ጉዳይ ላይ አንድ የሕግ ባለሙያ ፕሮፌሰር ይስሀቅ ኤፍሬም እና አትሌት ሀይሌ ገብረ ሥላሴ አርቲስቱን ከዚህ ቀደም እስር ቤት ድረስ ሄደው ልክ ከዚህ ቀደም በቅንጅት መሪዎች ላይ እንዳደረጉት ማነጋገራቸውን እንደ አንድ ምክንያት; እንዲሁም ዳኛው አቶ ልዑል ገብረማርያም የሕወሓት/ኢሕአዴግ አባል መሆናቸውን በማውሳት ቴዲ ከፍርዱ በሗላ ልክ እንደቅንጅት መሪዎች በይቅርታ ሰበብ ሊፈታ ይችል ይሆናል የሚል ግምታቸውን ሲሰጡ; በርካቶች ቴዲ አፍሮ የአንካሳው ሕግ ሰለባ ሆኖ ፍርዱን ጨርሶ ነጻ ይወጣል የሚል እምነት አላቸው። ይሄው ዳኛ ከ7 ዓመት በፊት በሞት እንዲቀጡ የወሰነባቸው 44የኦነግ አባላት ሰሞኑን በፕሮፌሰር ይስሃቅ እና ፓስተር ዳንኤል “አማላጅነት” በይቅርታ ሰበብ ከእስር መለቀቃቸው ይታወሳል። እነዚህ የኦነግ አባላት ሁለተኛ ወደፖለቲካ አንገባም ሕዝብንም እንዳይሳሳት እንቀስቅሳለን ብለው በመለስ ዜናዊ ሚዲያ ðላይ እየተናገሩ ይገኛሉ።