Thursday, December 4, 2008

ሃበሻ በሱዳን

ሱዳን ላይ ውሃ ሲጠማህ የምትጠጣው ከዚህ እንስራ ቀድተህ ነው.... ምናልባት ትል እ ና ትናንሽ እንቁራሪቶች ሊገኙበት ቢችሉም ውሃ ስለሚጠማህ ብቻ ዝም ብለህ መጠጣት ነው.....

ሐበሻ በሱዳን - ከሔኖክ ዓለማየሁ




ሰው በተለያየ አጋጣሚ ይሰደዳል:: እኔ ስደትን በሁለት አይነት እከፍለዋለሁ:: አንደኛው የቅንጦት ስደት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአስገዳጅ ሁኔታዎች የሚከሰት ስደት ነው :: የቅንጦት ስደት በኢትዮጵያ ሀገሩ መኖር እየቻለ የምእራብያውያን ናፋቂ የሆነው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ብዙሀኖቻችንን የሚወክል ይመስለኛል:: ጥቅምት 22/1997 አ .ም ነበር ከኢትዮጵያ የወጣሁት :: በዚህ ቀን ከሀገሬ ከመውጣቴ በፊት አንድ ነገር በጣም አስገርሞኛል:: እሱም የኢትዮጵያን ደህንነት አሰራር የታዘብኩበት ነው:: ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በጣም ይፈለግ ስለነበር በኤርፖርትም በድንበርም ከሀገር እንዳይወጣ ስሙ ተላልፎ ነበር:: ለጊዜው ስሙን ወደማላውቀው ሀገር አንድ አውሮፕላን ይነሳል:: በዚህ አውሮፕላን ላይ እስከዳር ነጋ የምትባል ሴት ተሳፍራለች:: አውሮፕላኑ እንደተነሳ አየር ላይ 20 ደቂቃ እንደፈጀ ተመልሶ እንዲያርፍ ተደረገ:: የኢትዮጵያ ደህንነቶች ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አመለጠን ብለው ተራወጡ:: መጨረሻ ላይ አውሮፕላኑን አስመልሰው ሲፈትሹ የተገኘችው ወ/ሮ እስከዳር ነጋ ናት:: እንግዲህ ይታያችሁ ወንድና ሴት መለየት የማይችሉ ስዎችን :: አውሮፕላኑን ደግመው ከማሳረፍ ከአየር መንገዱ የበረራ ሪፖርት መመዝገቢያ ላይ የሴትየዋን ማንነት ማረጋገጥ ይሻላል ወይስ?....
በዚህ የተነሳ የመተማን ድንበር አቋርጬ ወደ ሱዳን ለመግባት ምንም ፍራቻ አላደረብኝም :: እንደነ ነዋይ ደበበ ''በገዳሪፍ ካርቱም'' የሚለውን ዘፈን እየዘፈንኩ ገዳሪፍን አልፌ ካርቱም ገባሁ::
ተወርቶ የማያልቅላት ዴም
ካርቱምና የሀበሻ ስም ከተነሳ 'ዴም ' አትቀርም :: ዴም ዛሬ አውሮፓ ውስጥ ከሚገኙ ሊቢያን ለረገጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሕይወታቸው አንድ ክፍል ናት ብል አላጋነንኩም :: ለምሳሌ እስኪ ዴም አዝመራን ; እማማ (ነብሳቸውን ይማር ከሞቱ አመት ሊሞላቸው ነው) የማያውቅ ማነው? በተለይ እማማ ቤት ግድግዳ ላይ ከተጻፉ የግድግዳ ላይ ጽሁፎች በተለይ የጨርቆስ አካባቢ ልጆች የሳቸው ድንበኛ ነበሩ :: እማማ ሥራቸው አንድ ትልቅ ቤት ተከራይተው ''ኬሻ በጠረባ '' ሊባል በሚችል አተኛኘት በቀን 2 የሱዳን ሊራ እየተቀበሉ የሚያሳድሩ ሴት ናቸው:: ካርቱም ላይ በሙቀት የተነሳ ከቤት ውጭ ስለሚተኛ ለሳቸው ገበያ በጣም ተስማሚ ነው:: ምክንያቱም ያቺን የሲባጎ አልጋ ማታ ማታ እየዘረጉ ያሳድራሉ:: በጣም የሚገርመው እማማ ቤት በአንድ ለሊት እስከ 60 ሊደርስ የሚችል ሰው ማደሩ ነው:: ''ትንሽ ጨቅጫቃ ናት ; ግን የዋህ ናት '' የሚል ስም ያላት አዝመራ ቤት ውስጥ ከተለጠፉ ጥቅሶች መካከል ይህን ጽፌ ነበር:-

“የአባትህን ገዳይ አትበቀለው ሱዳን ካርቱም አምጥተህ ያለ ሀዋላ ጣለው”

ይህ ጥቅስ የሚያሳየው የካርቱም የሀበሻ ኑሮ ምነኛ አስቀያሚ እንደሆነ ያሳያል:: ከምግብ ውስጥ ርካሹ ፉል ነው ሱዳን ውስጥ ይህ የሚጠፋበት ጊዜ ብዙ ነው:: ለብዙዎቻችን ፉል እንኳ መግዢያ የሱዳን 50 ሳንቲም (ጅኔ) ይጠፋል:: እናም ይህን ለማሳየት ነው ጥቅሱ የተጻፈው:: ካርቱም ላይ እጅግ ታዋቂ ከሆኑ ሰዎች ሁለቱን ከጠቀስኩ ከዴም ጀምሮ ; ከሰሀፋ ዘለጥ እስከ ጅሬፍ; ከአባሁማማ እስከ አንዱርማን እና ሌሎችም ሰፈሮች የቃረምኳቸውን ታሪኮች ተራ በተራ ላስነበብ ::
ሣራ
ሣራ የብዙ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች መጠሪያ ስም ነው ካርቱም ላይ:: አንዷን ሴት አግኝተህ ማነው ስምሽ ብትላት ሣራ ትልሀለች:: ለምንድን ነው ዋና ስምሽን የምትቀይሪው ስትላት 'ለአጠራር እንዲመች' የሚል ተልካሻ ምክንያት ያቀርቡልሀል:: ዋናው ምክንያታቸው ራሳቸውን ለመደበቅ እንደሆነ የታወቀ ነው :: ራሳቸውን ከማን ይደብቃሉ ? እንዳትሉኝ :: ዛሬ ሳራ የሆነቸው ሴት ነገ 'ሀያት ' ከነገ ወዲያ 'ኢማን ' ይሆኑላችኍል :: ለምን ስማቸውን ይቀይራሉ? በቀጣይ ዘገባዎቼ መልስ ታገኛላችሁ :: በዚህ የተነሳ የሱዳን ሰዎች ኢትዮጵያዊ ሴት ሁሉ ሣራ ይመስላቸዋል:: አንዲትን ኢትዮጵያዊትን ሴት መንገድ ላይ ሲጣሩ እንኳ ሣራ ነው የሚሉት በብዛት::
ተክለሀይማኖት አካባቢ እንደተወልደች የምትናገረው ሣራ የሱዳንን ምድር ከረገጠች 2 አመት ሊሞላት የቀናት እድሜ ብቻ ነበር የቀሯት :: ለምን ወደ ሱዳን መጣሽ? ነበር ያልኳት - የምትሰራበት የላስቲክ ሻይ መሸጫ ቤት ውስጥ ገብቼ ቁጭ ካልኩና ብዙ ከእርሷ ጋር ከተግባባው በኍላ:: 'ከዚህ ቀደም በሌላ አረብ ሀገር ነበር የምኖረው :: የአረብ ገረድ መሆን መረረኝ:: እስኪ የአውሮፓን ሕይወት ልይ ብዬ ወደ ሱዳን መጣሁ' ስትል ትረካዋን የጀመረችው ሳራ 'ወሬውን የሰማሁት አዲስ አበባ እያለሁ ነው :: ብዙ ስዎች ሱዳንን አቋርጠው በሊቢያ በኩል ወደ ጣሊያን ይገባል ሲሉ ሰምቼ መጣሁ .: ከእኔ ጋር የመጣች ልጅ አሁን ሊቢያ ትገኛለች እኔ እድሌ ሆኖ ሱዳን ቀረሁ ' አለችን በቁጭት:: ለሳራ ሊቢያ መግባት ትልቅ ስኬት ነው:: ሊቢያ ምን ስቃይ ይኑር ; ይሙቅ ይድላ የምታውቀው የላትም:: ብቻ እሷ ሰዎች ያንን መንገድ ተጠቅመው ጣሊያን ስለሚገቡ ብቻ ሊቢያ የስኬቷ ምንጭ ነው::
ጥያቄዬ አላቋረጠም 'ለምን አልሄድሽም ታዲያ ?' አልኳት :: እምባዋ በአይኖቿ ጎን ብቅ ማለት ጀመሩ :: ታሪኬ ብዙ ነው ተወኝ አለችና እንደመመናቀርም ብላ ወደ ጓዳ ገባች:: በጣም ጓጓሁ:: ልጅቷ አንድ የተደበቀ ምስጢር አላት አልኩ:: ታዲያ ይህን ለማግኘት የግድ እርሷን መቅረብ ይገባኛልና ቀረብኳት:: ከብዙ ውትወታ በኍላ ልጅቷን 'አማራት' (street) 41 የሚባለው ሰፈር የሚገኘው ጋልፍ መዝናኛ ቀጠርኳት:: ሱዳን ላይ በተለይ ሴት ልጅ ጋር ቀጠሮ የምትይዘው እሑድ (አሀድ) ወይም ጁምአ (አርብ) ነው:: እነዚህ ሁለት ቀኖች ብዙ ኢትዮጵያዊያን ኢጃዛ (እረፍት ) የሚወጡበት ቀን ነው::
...ለምን ቀጠሮውን አረፈድሽ አልኳት ብዙ እንዳስጠበቀችኝ ለማስገንዘብ :: 'ሴትየዋ ጨቅጫቃ ናት :: ቶሎ አትለቀኝም:: አሁንም አኩርፋ ነው የመጣሁት:: እኔ ከቤት ስወጣ አትወድም::' የትኛዋ ሴትዮ ብዬ ሳልጠይቃት የምትሰራበት በላስቲክና በሸምበቆ የተወጠረው ሻይ ቤት የሌላ ሀበሻ ሴት ንብረት እንደሆነና እሷ በቀን 10 የሱዳን ዲናር እየተከፈላት እንደምትሰራ ነገረችኝ:: 'አየህ ሱዳኖች ወንዶቹ የኛን ሴቶች ይፈልጋሉ:: የኛን ሴቶች ለማየት ሲፈልጉ ወደሻይ ቤታችን ይመጣሉ:: ሻይ ፍለጋ ሳይሆን እኛን ::' የምትለው ሳራ ወደ ሻይ ሥራ ለምን እንደገባች ስታስረዳ:: ታሪኩ ብዙ ነው ትላለች ::
በወር 150 ዶላር ደመወዝ ይከፍልሻል ብለው ወደሱዳን ያመጡዋት አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ደላሎች ናቸው:: ለሱዳን 5 ሺህ ብር ክፍላ መምጣቷ ሳያንስ በሱዳን አሰሪዎቿ የደረሰባት ነገር እጅግ ያሳዝናል:- 'አንድ ቀን ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ እንደወትሮዬ ከሁሉም ቀድሜ ተነስቼ ቤቱን የማጸዳው እኔ ስለነበርኩ አይኔን ሳልገልጥ ስወጣ ቤቱ ደጃፍ ላይ ድመት ታርዶ አንገቱና ሰውነቱ ተለያይቶ ተጥሎ አገኘሁ ....'
''የታረደውን ድመት እንዳየሁ አዞሮኝ ወደቅኩ:: ከዛ በኍላ ራሴን ያወቅኩት ከአንድ ቀን በኍላ ነው:: የሴትዮዬ (ማዳሟን ነው) ባል ከአጠገቤ ተቀምጦ ነበር :: ከዛም የሆነውን ሁሉ ጠየቅኩት :: ድመት አርደው በር ላይ እንዲጥሉ ያደረጋቸው እምነታቸው እንደሆነ ነገረኝ '' የምትለው ሳራ ከዛ በኍላ ራሷም የእምነቱ ተከታይ በመድሐኒት እንዳደረጓት እምባዋ እየወረደ ነገረችኝ::
ሱዳን በሳይንስ የተረጋገጠ መረጃ ባላገኝም እንደሚወራው ከሕንድ ቀጥሎ ሁለተኛዋ የባድ ስፕሪት (ጠንቋይ) ሀገር ናት:: ሙአሰላት (አውቶቡስ) ውስጥ እየሄድክ ከአጠገብህ ጀለቢያ ያደረገ ቁመተ ረዥም ሱዳኒ ማግኘት የአፈር ያህል ነው:: ይህን ሱዳን ትንሽ እንዳወራህው ስለ ግል ህይወቱ ብትጠይቀው ጥንቆላ እንዳለበት ካለምንም ማፈር ይነግርሀል::
አንድ ቀን የሀበሻ ምግብ ቤት ውስጥ ቁጭ ብዬ በምሰማት ጥቂት አረብኛ ቋንቋ አንዱ ጠብደል ሱዳን ለኛ ሴት ክንዱ ላይ በቁልፍ የታሰረ ቀበቶ ያሳያታል:: እሱም ይህን እያሳያት የሚነግራት ነገር ያሰረው በቁልፍ የታሰረው ቀበቶ ማንኛዋም ያናገራት ሴት እንድታፈቅረው እንደሚያደርግ እና ጥይት ቢተኮስበት እንኳን ይህ እንደ ሚከላከልለት ሲነግራት ስምቻለሁ:: ልክ እንደዚሁ ሁሉ ሱዳን ውስጥ ስለ ጥንቆላ ማውራት በጣም አይቸግርም::
ይህን ስል ሱዳን ያሉ የእኛም ሰዎች ጤነኛ ናቸው ማለት አይደለም:: አብዛኞቹ ቀን ቀን ካርቱም መድሐኒአለም ማታ ማታ ሱቀል ዴም ያለው ጠንቋይ ቤት አይጠፉም:: ብዙሀኑን የሀበሻ የላስቲክ ቤት ሻይ ቤቶች ስትጎበኙም መሬቱን ስታዩ ጥቁር አዝሙድ ተንስንሶ ታያላችሁ :: ጥቁር አዝሙድ እና ጥንቆላ ምን አገናኘው ብዬ ጠይቄ ግን ምላሽ ማግኘት አልቻልኩም :: **** **** ***** እምባሽን አቁሚ ብዬ እያባበልኩ ጨዋታዋን እንድተቀጥልልኝ አደረግኩ ::
ሱዳንና ሱዳናውያንን እየቃኘን ነው:: የኛ ሰው በሱዳን ምን እንደሚመስል እያየን ነው:: አብዛኞቹ በባእድ አምልኮ ወደውም ይሁን ሳይወዱ እንዴት እንደሚገቡ ለማሳየት እየሞከርኩ ነው:: ሳራ በታረደ ድመት ዞሮባት የባእድ እምነቱን መከተል ጀምራለች:: ''ከወደቅኩበት እንደተነሳው የተነገረኝ ነገር ቢኖር ያዳነኝ አምላክ ድመቱ የታረደለት እንደሆነ ነበር '' ያለችኝ ሳራ የአሰሪዋ እናት በካርቱም ታዋቂ ጠንቋይ እንደሆኑ አስረግጣ ነገረችኝ::
ከዛስ? 'ከዛማ ወደ አባይ ወንዝ (ካርቱምን የሚያቋርጠው) መሄድ ጀመርኩ :: አንድ ምሽት ሴትዮዬ ልጃቸው እና እኔ ሆነን ወደ ባህር ሄድን :: ከሌሊቱ 6 ሰአት አካባቢ ነው:: ባህሩ ከምሰራበት አንዱርማን የ 30 ደቂቃ መንገድ ቢኖረው ነው:: እዛ ሄደን ከመኪናው እንደወረድን ሴትዮዬ ቀድማ ወደ ባህሩ ተጠጋች :: ከዛም መኪናው ውስጥ ከያዝነው የተቀጣጠለ ክሰል ጋር እጣን ነስንሳ ወደ ባህሩ ጋር ተጠጋች :: የሚሆነው ነገር ሁሉ በጣም እያስገረመኝ መጣ:: ሴትዬዋ ተንበርክካ እያለቀሰች አንዳንዴም እያጓራች እጣኑን ወደባህሩ ይዛው ትንሽ ገባ አለች:: የዛን ጊዜ ከወንዙ ውስጥ ያሉት አሶች ወደላይ እየዘለሉ እየወጡ ሲገቡ ተመለከትኩ :: በጣም ደነገጥኩ :: አጠገቤ ያለው ልጃቸውና ሚስቱ ተንበርከክው ማጉዋራት ጀመሩ:: ራሴን ስቼ ወደቅኩ'' በሚል ታሪኳን ተረከች:: ተመስጬ እያዳመጥኳት ነው::
''ከሁለት ቀን በኍላ ነው የነቃሁት:: ሴትዮዬ ስነቃ ወደ እኔ መጥታ ከአሁን በኍላ እኔ ቤት ሥራ አትሠሪም:: የባህሩና የድመቱ አምላክ ላንቺ የሚሆንሽን ሰው መርጦልሻል'' ብላ ከአንድ ሀብታም የዚህ ባእድ አምልኮ ተከታይ ሱዳን እንዳጋባቻትና ከዚህ ሰው ጋር አብራ ለጥቂት ጊዜ እንደኖረች ነገረችኝ:: ከዛም ይህ ሱዳን እሷን የሚፈልገውን ያህል ከተጫወተባት በኍላ ለሥራ ቤቱ ከተቀጠረች ሌላ ኢትዮጵያዊት ጋር ግንኙነት ጀምሮ በእኩለ ሌሊት ከእቤት እንዳስወጣት ጨምራ እያለቀሰች ነገረችኝ::
የምትነግረኝ ነገር ስሜቴን እየጎዳው ነው :: በዛ ላይ የምታነባው እምባ በጣም ልብን ይነካል :: ሰው መሆንንና መፈጠርን ሁሉ ያስመርራል :: መጨረሻዋ ሻይ ቤት መሥራት ይሁን እንጂ እዚህ ላይ እንዴት እንደደረሰች ጠየቅኳት ::
''አንዱርማን የሚኖሩ ሀበሾች አብዛኞቹ የተጣባቸው ባእድ አምልኮ ስላለ እነሱ ምንም ይረዱኛል ብዬ ሳላስብ ወደ ካርቱም መጥቼ ዴም ያሉ ሀበሾች ይረዱኝ ዘንድ መጣሁ :: እዛ እንደመጣሁ ወደ ሊቢያ የሚሄዱ የአዲስ አበባ ልጆች አገኘሁ :: ስምሽ ማነው ሲሉኝ ቤቲ አልኳቸው :: ስሜን ለሦስተኛ ጊዜ መቀየሬ ነው:: የደረሰብኝን ሳልነግራቸው አዲስ መጤ እንደሆንኩና ሱዳንን ምንም እንደማላውቅ ብሎም ገንዘብ እንደሌለኝ እያለቀስኩ ነገርኳቸው :: አዘኑና እኛም ቤት የለንም :: ቢሆንም በቀን ሁለት ብር እየከፈልን የምንኖረው አዝመ ራ ቤት ነው:: ሥራ እስከምትጀምሪ ድረስ እኛ የምንበላ ውን ፉል እየበላሽ ትኖሪያለሽ; የአልጋም እንከፍላለን አሉ::
''ከእነሱ ጋር ለ3 ቀናት ያህል እንደተቀመጥኩ 'ማዳም ቤት' (የሰው ቤት ሥራ ማለት ነው ) ሥራ አገኘሁ:: ቢቸግረኝም አልሰራም አልኩ:: ልጆቹ ለምን አሉ? ሥራ አትወጂም ማለት ነው ብለው የሚያስከፋ ቃላትን ሰነዘሩብኝ:: እኔ ማዳም ቤት ሥራ አልሰራም ያልኩት የደረሰብኝ አሰቃቂ አደጋ እንዲደገም ስለማልፈልግ እንጂ ለሌላ አልነበረም :: ቢሆንም ልጆቹ ጥሩ ነገር ቢያደርጉልኝም ስሜቴ ቶሎ ስለሚጎዳ ትቼ ወጥቼ መንገድ ላይ ስሄድ አንድ ሀበሻ አግኝቶኝ እኚህ ሴትዮ ቤት ሥራ አስገባኝ '' አለች የቀድሞዋ ሣራ የአሁኗ ቤቲ::
በጣም የሚያሳዝነው የቤቲ ሕይወት ከድጡ ወደማጡ ነው :: ከሱዳን ቤት የወገኔ ቤት ይሻለኛል ብትልም እኚህም ሴት ያው ናቸው :: ለምሳሌ አንድ ቀን እሳቸው ቤት ሻይ ልጠጣ ከካርቱም ጓደኞቼ ጋር ገብቼ ሳላውቅ አንድ ጥግ ስር የጎዘጎዙትን ሳር : የበተኑትን ጥቁር አዝሙድና ፈንዲሻ ረግጭባቸው ሁለተኛ እዚህ ቤት እንዳትደርስ ብለው አባረውኛል :: ግን ዝንጉ ስለሆኑ በሌላ ቀን ስሄድ አስገብተውኛል ::
''በቀን 5 ጊዜ ለአሮጊቷ ቡና ማፍላት አለብኝ:: ጠዋት የላስቲክ ቤቱን ሻይቤት ከመክፈቴ በፊት እግሯን የተቆረጠች እርግብ አለቻቸው:: ለእርሷ ስንዴ መበተን አለብኝ:: ያንን ባላደረግኩ ቀን ገበያ የለም:: ቤቱ ጭር ብሎ ይውላል:: ታዲያ ማታ ሂሳብ ስንሰራ ሂሳቡ ሲያንስባቸው አሮጊቷ አያስቀምጡኝም : ለምን ለእርግቧ ስንዴ አልበተንሽም ; ለምን ጥቁር አዝሙድ መሬቱ ላይ አልነሰነስሽም በሚል ብዙ ውርጂብኝ ያወርዱብኛል '' ብላኛለች:: ያው የእኔ ሥራ ከማዳመጥ በቀር መጠየቅ ነውና ለምን ታዲያ ቤቱን ለቀሽላቸው አትወጪም ስላት ''ምን እንዳዞሩብኝ አላውቅም አንዲትም ቀን ቤቱን ስለመልቀቅ አላስብም :: የምፈልገውን ቢዝነስ አገኛለሁ'' አለችኝ :: ቢዝነስ በካርቱም ሌላ ትርጉም አላት :: አብዛኞቹ ሻይ ቤት የሚሰሩ ሴቶቻችን ቢዝነስ አላቸው:: ምን? (ሐበሻ በሱዳን..... በቀጣዩ እትም ይቀጥላል።)

No comments: