
''ይህው ደረትሽ ነው ያጣላኝ ሁሉን !' እስኪ ሽፈን አርጊው ያ ጡት እንደሆን !!'
ይህን ስንኝ የሚረሳ ማነው ? በኢትዮጵያ ራዲዮ ከምሽቱ አራት ሰአት በኍላ የሚተላለፉ የታምራት የሙዚቃ ክፍለጊዜዎች ላይ ሳንሰማቸው የቀረንባቸው ጊዜያት አሉ ? ''ተማር ልጄ '' የምትለውን ሙዚቃም አንረሳም :: እናትና አባቶቻችን በትምህርታችን እንድንበረታ ይህችን ዘፈን እያቀነቀኑ አልመከሩንም ?... የዛሬው የመጀመሪያው ዝግጅቴ ተወዳጁና ተናፋቂውን አርስቲስት አለማየሁ እሸቴን ያስቃኛል :: መልካም ቆይታ :-
ከሊሊ ሞገስ
(የሐበሻ ጋዜጣ ልዩ ጸሐፊ)
''ኢትዮጵያዊ ኤልቪስ ፕሪስሊ '' ይሉታል የዛ ዘመን ሰዎች :: በሙዚቃ ሥራው በዛም ዘመን በእኛም ዘመን አዲስ ና ልዩ እንዲሁም የራሱ ፈጠራ ያለው ሰው ሆኖ እዚህ ደርሷል :: ''አዲስ አበባ ቤቴ ... አዲስ አበባ ቤቴ ሸጋ ልጅ ቆንጆ ልጅ አለች ጎረቤቴ ''
ታዋቂው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ''አለማየሁ እሽቴን እንዴት አድርገህ ትገልጸዋለህ ?'' በሚል መነን በሚባል መጽሄት ለቀረበለት ጥያቄ ትንሽ ቆም ብሎ በማሰብ ''ሦስት ነግሮች አሉት '' ሲል ይጀምራል :: ''አለማየሁ የራሱ የሆነ ፈጠራ አለው :: ከሁሉም ዘፈኞች ወጣ ያለ ባህሪ እንዲኖረው ይፈልጋል :: ከዚህም በላይ ለአዲስ ነገር ቅርብ ነው '' ሲል ይገልጸዋል :: ይህ የጥላሁን ገለጻ በእርግጥም ትክክል ነው :: በሾላ አካባቢ በገዛው መሬት የሚኖረው አለማየሁ እሸቴ አብዛኞቹ የሙያ አጋሮቹ ትዳር እና ሴት ሲቀያይሩ እስኩ ግን እሳካሁን በአንድ ሴት እንደጸና አለ :: በሁለተኛ ደረጃ ለአዲስ ነገር ቅርብ ነው ለሚለው የመጨረሻ ካሴቱን መመልከት ይቻላል :: ከ 2 አመት በፊት በአምባሰል ሙዚቃ ቤት አማካኝነት ያወጣው ካሴቶ እጅግ ተወዳጅ የነበረ ሲሆን በክሊፑም ዘንድ የተዋጣለት መሆኑን አሳይቷል :: በ 3ኛ ደረጃ አሌክስን ልዩ የሚያደርገው ራሱን ከዘመኑ ጋር መለወጡ እና በቆመበት አለመቅረቱ ሲሆን ዘፈኖቹ ከምንም በላይ በምክር እና በትምህርት ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉ ላይ ነው::
''ወደ ሙዚቃው ሙያ ለመግባት መሰት የሆነኝ ለኤልቪስ ያለኝ ፍቅር እና ክብር ነው '' የሚለው አለማየሁ ወደ ሙዚቃው ሕይወቱ ሲገባ በቤተሰቦቹ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ጫና ነበረበት :: በተለይ አባቱ ከሽመል በበለጠ እስከ ጠምንጃ መምዘዝ የደረሱበት ጊዜ ነበር ያኔ :: የዛ ዘመን ሰው ሙዚቀኛን እና ወርቅ አንጣሪን እንዴት ይመለከት እንደነበር ማስታወሱ በቂ ነው:: አለማየሁ ይቀጥላል::
''... በተለይ አባቴ በሙዚቃ ሕይወት ውስጥ ጠልቄ መግባቴን አልወደደልኝም :: ስዘፍን ውዬ ስመጣ ማምሻውን እቤቴ ዱላ ይጠብቀኛል :: የዛን ጊዜ የምንሰራው ለገንዘብ ሳይሆን ለሙያ ፍቅር ነበር :: እናም አንድ ዘፈን አወጣሁ :: ያ ዘፈን :- የሴት ልጅ ከመባል ዘወትር የሚል ነበር :: ይህ ዘፈን መልእክቱ አባት መሞት እንደሌለበት : አባት ከሞተ ልጅ የሴት ልጅ ... ቀማኛ ... ዱርዬ ተብሎ እንደሚሰደብ መልእክት ያለውና የአባትን ጥቅም አጉልቶ የሚያሳይ ነበር :: እናም አባቴ ይህን ዘፈን በራዲዮና በሽክላ ሲሰማ ለሙያዬ ልዩ ፍቅር አደረበት :: መኪና ገዝቶ ሰጠኝ :: ከዛም ያበረታታኝ ጀመር ''
የአለማየሁ የሙዚቃ ሕይወት ጅማሮ ይህን ሲመስል በሙዚቃው ሕይወቱ እውቅናው በመላው ኢትዮጵያ እየተሰራጨ በመጣበት ወቅት በምጽዋ በኩል ጠፍቶ ወደ ሆሊውድ በባህር ጠፍቶ ሊሄድ ሲል ተይዞ መመለሱን ያስታውሳል :: ''ያኔ ወጣት እያለሁ ወደ ሆሊውድ መሄድ ፈልጌ ነበር :: ይህ ህልሜ ቢያሳካ ኖሮ በአለም ላይ ታዋቂ ሰው እሆን ነበር '' ይላል - አሌክስ ::
ከአለማየሁ እሽቴ ጋር በጋራ ለመዝፈን እድሉ ካጋጠማቸው አርቲስቶች መካከል አንዷ ድምጻዊት ኩኩ ሰብስቤ ነበረች :: አርቲስቷ ለአለማየሁ ያላትን ክብር የምትገልጸው በቃል ብቻ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም :: ''አለማየሁ '' ትላለች ''ዳንሱና የዘፈን ግጥሞቹና መልእክቶቹ ደስ ይሉኛል '' ትላለች :: አድናቂው እንደሆነች የምትናገረው ኩኩ አብራው በመዝፈኗ እድለኛ እንደሆነች ጭምር ታብራራለች::
በአራዳ ፒያሳ አካባቢ የቆርቆሮ የሙዚቃ ባንድ ሰርተው የሙዚቃ ጥማቸውን እጃቸው ላይ ልክ ማይክ እንዲመስል እንጨት ወይንም ማንኪያ ይዘው እየዘፈኑ ሙዚቃን የጀመሩት አሌክስና ጓደኞቹ እሱ በሙዚቃው ሥራውን አንቱታን ሲያተርፍ ሌሎቹ ግን በሌላ ሥራ ላይ እንደተሰማሩ ይናገራል :: በግልጽነቱና በትዳሩ ታማኝነቱ በምሳሌነት ከአርቲስቶቻችን የሚጠቀሰው አሌክስ :- በ 1955 ፖሊስ ኦኬስትራ ውዝዋዜ ለመቀጠር /ለመሰልጠን / ሄዳ ፍቅር የሸመተችው እጅጋየሁ እስከዛሬ የአለማየሁ እሸቴ ሚስት ነች ::አለማየሁ እንደ አርቲስት ቀበጥ አይደለም ማለቴ ሲያገባ ሲፈታ የኖረ አይደለም:: ትዳሩን አክባሪ ነው ::በአንድ ወቅት ለትዳሩ እና ለልጆቹ ያለውን አመለካከት ሲነግረኝ ''ለሚስቴም ሆነ ለልጆቼ ያለኝን ፍቅር የሚተካውም ሆነ የሚለውጠው ምንም የለም ::ያለኝን ትርፍ ሰአት ከእነሱ ጋር ባሳልፍ ደስተኛነኝ ""ነው ያለኝ::
''አሁንም ቅድምም ታሽካካለች ዶሮ እኔ አንቺን ማግኘቴ ሕልም ነው ዘንድሮ አዲስ አበባ ቤቴ አዲስ አበባ ቤቴ ሸጋ ልጅ ቆንጆ ልጅ አለች ጎረቤቴ አረ እንዳው ይመኙሻል አረ እንዳው ይመኙሻል በምኞት ቢጓዙ ወዴት ያገኙሻል ''
እኚህ በፎቶ ግራፍ ላይ የምትመለከ ቷቸው ግለሰብ አምሀ እሸቴ ይሰኛሉ :: አምሀ እሸቴ የአባታቸው ስም ከአሌክስ አባት ጋር ሲመሳሰልባችሁ ወንድሙ እንዳይመስሏቸው :: ይልቅዬ በዛ ዘመን ታዋቂ የሙዚቃ አሳታሚ ነበሩ :: በ 1944 የመጀመሪያ የሸክላ ካሴቱን ለሕዝብ ሲያደርስ ሸክላውን ያሳተሙለት እኚሁ ግለሰብ ነበሩ :: አምሀ እሸቴ የሙዚቃ አሳታሚ የሚል ድርጅት የነበራቸው እኚሁ አባት ዛሬ በህይወት አይኑሩ እንጂ ከጥላሁን ገሰሰ ጀምሮ በዛ ዘመን የነበሩ ዘፈኞችን ዘፈኖቻቸውን በሽክላ አሳትመውላቸዋል:: በሙዚቃ ሕይወቱ ከአንድ መቶ በላይ ዘፈኖችን ለሕዝብ ያደረሰው አለማየሁ እሸቴ እስካሁን በካሴትና በሲዲ የሰራቸው ዘፈኖቹ 8 ብቻ ናቸው::
''ኢትዮጵያዊ ኤልቪስ ፕሪስሊ '' አለማየሁ እሸቴ ከአማርኛ ሙዚቃዎች ሌላ የእንግሊዘኛ ሙዚቃዎች የሚዘፍን ሲሆን በተለይም አረብኛ ሙዚቃዎችን በሱዳንኛ ዜማ ይዘፍናል:: ከዚህም በተጨማሪ ሱማሊኛ ይዘፍናል:: አሁን ባለው ሥርአት በእጅጉ የማይወደደው አለማየሁ ለዚህ ምክንያቱ እንደ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች በተለያዩ የተቃዋ ሚ ፓርቲዎች መድረክ በተለይም በአብዮት አደባባይ ከሕዝብ ጋር ለተቃውሞ መውጣቱ በገዢው መደብ ሰዎች ጥርስ እንዲነክስበትና አንዳንድ ጫናዎችም እንዲደረጉበት ሆኗል ::
''ማን ይሁን ትልቅ ሰው ማን ይሁን ትልቅ ሰው ማን ይሁን ትልቅ ሰው ማ .................ን ይሁን ትልቅ ሰው ያንዱን ቁጅ አንደኛው ሲያኮስሰው ማን ይሁን ትልቅሰው .... ያንዱ ቤት ሲጎድል አንዱ እየተረፈው ክፉና ደጉን ዘመን ካሳለፈው እኔ ግን መራመድ ከቶ አልቻልኩም ገና ትኋን !... ትኋን ደሜን መጦ ደሜን መጦታልና ጊዜው ጎዳኝ እንጂ እኔ ሰው አላማም ዋ ... ያህያ ልጅ በቅሎ ወርቅ ተሽልማ ብናገር ወረኛ ባለጌ ይሉኛል ብቻ ግን በሆዴ ቢቀር ይሻለኛል !!
የአሌክስን ይህን ተወዳጅ ሙዚቃ በድምጹ ሲያንቆረቁረው ለመስማት http://www.ethiopianow.com/music/alemayehu/ ላይ 13ኛውን ሙዚቃ ያዳምጡ:: አለማየሁ እሸቴ ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል:: በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላውን ጥበብ አብረን እንቆነጥራለን::ð
No comments:
Post a Comment